የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በ2019 በጀት ዓመት ባለፉት ሶስት ወራት 138 ሺህ 736 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረጉን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጌቱ ገረመው አስታወቁ።
በሩብ ዓመቱ ከአዳዲስ ደንበኞች መካከል 123 ሺህ 509 የሚሆኑት የቅድመ ክፍያ፣ 15 ሺህ 227 ደግሞ የድህረ ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚዎችእንደሆኑ ተጠቁሟል።
አዳዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወነው ሥራ፣ ከዋናው የኤሌክትሪክ ግሪድ 21፣ ከኦፍግሪድ ውጭ ደግሞ 9 ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ሆነዋል።
አፈጻጸሙም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ15.4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
ለነባር ደንበኞች አስተማማኝ የኃይል አቅርቦትን ለማረጋገጥ 630 ኪሎ ሜትር የዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ መልሶ የግንባታ እንዲሁም 275 የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮችን የማሻሻል ሥራ መከናወኑንም ኢንጂነር ጌቱ ጨምረው ገልጸዋል።
አዳዲስ ደንበኞችን እንዲሁም የገጠር ከተሞችና መንደሮችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ 1 ሺህ 730 ኪሎ ሜትር የዲስትሪቢዩሽን ኔትወርክ ማስፋፊያ እንዲሁም 1 ሺህ 329 አዳዲስ የዲስትሪቢዩሽን ትራንስፎርመሮችን የመትከል ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።
ተቋሙ ብልሹ አሠራርን ለመከላከልና ተጠያቂነትን ለማስፈን እየሠራ እንደሚገኝና በዲጂታልና በሌሎች አማራጮች 96 ጥቆማዎችና አቤቱታዎች ቀርበዋል።
በተከናወነ ምርመራም 42 ሠራተኞች ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል። በዚህም የተለያዩ የዲሲፕሊን እርምጃዎችየተወሰዱ ሲሆን 19 ሰራተኞች የደመወዝ ቅጣትና 1 የሥራ ስንብት እርምጃ ተወስዷል።
ለተቋሙ በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት ወርሃዊ ሂሳባቸውን የሚከፍሉ ደንበኞች መጠን 95.3 በመቶ እንዲሁም አጠቃላይ ደንበኞች ብዛት 6.03 ሚሊዮን ሊደርስ ችሏል።SECO


