ኢትዮጵያ በ2018 በጀት ዓመት መጀመሪያ በሦስት ወራት ውስጥ ከቡና ወጪ ንግድ 762 ነጥብ 75 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቷ ተገለጸ። ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ ያለው መሆኑ ተጠቁሟል።
የባለሥልጣኑ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ተስፉ አለማየሁ እንደገለጹት፤ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ 113 ሺህ 542 ቶን ቡና ወደ ተለያዩ የውጭ ሀገራት ተልኳል።
ከተላከው ቡና 762.75 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ የተገለፀ ሲሆን የተገኘው ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 243 ነጥብ 73 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አልዉ ተብሏል።
ኢትዮጵያ የቡና ምርቷን በዋናነት ወደ ጀርመን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ቤልጄም እና ሌሎች ሀገራት በመላክ የውጪ ንግዷን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደገች መሆኑን አቶ ተስፉ አክለው ገልጸዋል።


