በኢትዮጵያ የጫት ቁጥጥር አዋጅ አለመኖር ለታዳጊ ወጣቶች ሱስ መባባስ ምክንያት መሆኑ ተገለጠ

በኢትዮጵያ ከጫት ጋር በተያያዘ እንደ አልኮልና ሲጋራ ግልጽ የሆነ የቁጥጥር አዋጅ አለመኖሩ፣ ለታዳጊ ወጣቶች ገና በአሥራዎቹ ዕድሜያቸው ለሱስ እንዲጋለጡ በር መክፈቱን የዘርፉ ባለሙያዎችና አስተያየት ሰጪዎች ገለጹ።

 በተለይም በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ጫት በግላጭ መሸጡ ችግሩን አሳሳቢ እንዳደረገው ተመልክቷል።

የጀርመን ድምፅ እንደዘገበው፣ በ14 ዓመቱ ጫት መቃም የጀመረው ጀማል ኢብራሂም የተባለ ወጣት መጀመሪያ ላይ ለንቃትና ለሥራ ተነሳሽነት ብሎ የጀመረው ሱስ፣ በኋላ ላይ የመማርና የመሥራት ፍላጎቱን እንዳሳጣው ምስክርነቱን ሰጥቷል።

 ሻጮች የተማሪዎችን ዩኒፎርም ሳይለዩ ገንዘብ እስካገኙ ድረስ ለሕፃናትም ጭምር ጫት እንደሚሸጡ ወጣቱ ተናግሯል።

የሕግ ክፍተትና የትምህርት ጥራት መውረድ

የተማሪዎች የሥነ-ልቦና አማካሪ የሆኑት ዙፋን ተስፋዬ እንደሚሉት፣ በግል ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ጫት ቤቶች በስፋት መከፈታቸው ተማሪዎች ከትምህርታቸው ይልቅ ለሱስ ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል።

“ሥራዬ ብለው ደጃፍ ላይ የጀበና ቡና በሚል ሽፋን ጫት የሚያቀርቡ ቤቶች አሉ” ሲሉ አማካሪዋ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የመቋሚያ ማኅበረሰብ ልማት ድርጅት መሥራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤልያስ ካላዩ በበኩላቸው፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተሳተፉበት አዋጅ የማርቀቅ ሥራ ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁን እንጂ የዕድሜ ገደብንና መሸጫ ቦታዎችን የሚወስነው ይህ ረቂቅ ሕግ እስካሁን ከፍጻሜ ሳይደርስ መቅረቱ ለትውልድ ውድቀት ምክንያት እየሆነ ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ኤልያስ ገለጻ ከሆነ 61 በመቶ የሚሆኑ አዳጊ ወጣቶች ጫት ስለሚያስከትለው የጤና እክል በቂ መረጃ የላቸውም። ይህም የብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር በትምህርት ጥራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል።

አሁን ላይ ጫት እንደ ፋሽን እየታየ በትምህርት ቤቶች አካባቢ በስፋት እየተሸጠ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል።

የጫት መስፋፋት በተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በግብርናው ዘርፍም ለውጥ እያመጣ መሆኑ ተገልጿል።

 የግብርና ባለሙያው አቶ አሰላፍ አሰን እንደሚሉት፣ አርሶ አደሮች የምግብ ሰብሎችንና ፍራፍሬዎችን በማጥፋት ወደ ጫት ተከላ እየተሳቡ ነው። “የተገነቡ የመስኖ መሠረተ ልማቶች ሳይቀሩ ወደ ጫት እርሻ እየተቀየሩ ነው” ያሉት ባለሙያው፣ መሬቱ የአርሶ አደሩ የግል በመሆኑ ለማስገደድ መቸገራቸውን ጠቁመዋል።

ጫት ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ምርት ቢሆንም፣ አጠቃቀሙንና ሽያጩን የሚቆጣጠር ሕግ ባለመኖሩ ምክንያት የሚከሰተው ማኅበራዊና የጤና ቀውስ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ እያመዘነ መሆኑን ዘገባው አመልክቷል።@seco

Related

ኢትዮጵያ ወደ ጠንካራ ፋርማሲዩቲካል ማምረት እየተሸጋገረች እንደሆነ ተገለጸ

ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት የደረጃ 3 (ML3) ያገኘች 9ኛዋ...

ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ ነፃ መሆኗ በይፋ ተበሰረ

ኢትዮጵያ ከማርበርግ ቫይረስ ወረርሽኝ ነፃ መሆኗ በይፋ ተበሰረ በኢትዮጵያ ተከስቶ...

Popular Categories