በአዲስ አበባ እና በሸገር ከተሞች ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ በ4.3 ቢሊዮን ብር 4ኛው ምዕራፍ የዲስትሪቡዩሽን መስመር መልሶ ግንባታና ዓቅም ማሳደግ ፕሮጀክት እያከናወነ እንደሚገኝ አገልግሎቱ አስታውቋል፡፡
703 ኪ.ሜ የዲስትሪቡሽን ኔትዎርክ መልሶ ግንባታና አቅም ማሳደግን ያካተተው ፕሮጀክቱ 2 ሺህ አዲስ የተለያየ አቅም ያላቸውን ትራንስፎርመሮች ተከላና 2 ሺህ ነባር ትራንስፎርመሮችን አቅም የማሳደግ ሥራ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡
በፕሮጀክቱ ከኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ወጪ የሚሆኑ 56 ማሰራጫ መስመሮችን መልሶ የመገንባትና የማሻሻል እንዲሁም ከተፈቀደው የኃይል አጠቃቀም በላይ ሲሆን መቆጣጠር የሚያስችሉ 62 የሎድ ብሬክ ስዊች ገጠማ ይያካትታል ተብሏል፡፡
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የፊዚካል ሥራው አፈፃፀም 36 ነጥብ 74 በመቶ የደረሰ ሲሆን 2 ሺህ 857 የኮንክሪት ምሰሶዎች ተከላ ስራም ተከናውኗል፡፡
ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአዲስ አበባና በሸገር ከተሞች በዓመት በ100 ኪ.ሜ የመካከለኛ የኃይል ማሰራጫ መስመር ላይ የሚከሰተውን የኃይል መቆራረጥ ድግግሞሽን በ27 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል፡፡ እንዲሁም የትራንስፎርመር መቃጠልን ከ3 ወደ 2 በመቶ ለመቀነስ ያስችላል ተብሎ ይጠብቃል።
የሚገነቡት የዲስትሪቡዩሽን መስመሮች በኮንክሪት ምሰሶና በሽፍን ኬብል በመሆኑ አደጋን ለመከላከልና ረጅም ዓመት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ወጪ 4.3 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ጠቅላላ ወጪው የሚሸፈነው ከአለም ባንክ በተገኘ ብድር እንደሆነ ቅዳሜገበያ ከአገልግሎቱ ያገኘችው መረጃ ያሳያል፡፡@SECO


