ሙሉቀን የወንድወሰን (ነፃ ሃሳብ)
ለኢኮኖሚ ወደብ ምን ማለት እንደሆነ እንዲገባህ አለፍ አለፍ እያልክ ወደ ጅቡቲ ና። ባለፉት 16 አመታት በደርዘን ለሚቆጠሩ ጊዜያት ወደ ጅቡቲ መጥቻለው።
ሁሉኑም በሚባል ደረጃ ወደ ትንሿ አገር ያቀናሁት ለወደብ ወይም ከመርከብ እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ነው።
በታጁራ አዲስ ወደብ ሲገነባ፣ በዶራሌ የተገነባ ሲመረቅ፣ የኮንቴነር ወደብ ማስፋፊያ ወደ ስራ ሲገባ ወይም እጅግ ዘመናዊ ወይም እገሌ የተሰኘች የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ መርከብ ቀባበል ሲደረግ፣ የሆነ ድርጅት ግዙፍ መርከብ ለመጀመሪያ ጊዜ በጅቡቲ መህልቋን ስትጥል ለመታደም አለያ ለመጎብኘት እድል ገጥሞኛል።

በነዚህ አመታት ስለጅቡቲ እና ኢኮኖሚዋ እንዳውቅ ብዙ እድል ተፈጥሮልኛል። ብዙ እንዳነብ እና እንድከታተል ጠቅሞኛል፡፡
በርግጥ በጣት በሚቆጠሩ ግለሰቦች ግብታዊ ውሳኔ ወደብ አልባ መሆናችንም የፈጠረብኝ ቁጭትም አነሳስቶኛል፡፡
የጅቡቲን እድገት እና ለውጧን ማስተዋል ይቻላል፡፡

አስደማሚ ነው!
የዛሬ አስራ 16 አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ጅቡቲ ስመጣ አንድ አነስተኛ እና የቅኝ ግዛት ዘመን ወደብ እንዲሁም ሌላ በዛው ሰሞን በዶራሌ አካባቢ የተገነባ አንድ የኮንቴነር ማስተናገጃ ነበራት አገሪቱ።
ሆራይዘን የሚባለው የነዳጅ ወደብም እኤአ በ2005 በዱባዮች ተገንብቶ የኢትዮጵያን ምርት ተቀብሎ ያስተናግድ ነበር።

ዛሬ በታጁራ፣ በጎቤት፣ በዶራሌ ተጨማሪ ወደቦች ስራ ላይ ናቸው።
በነፃ ቀጠናቻው በርካታ ኩባንያዎች ገብተዋል፡፡
ከ57 አገራት የመጡ ከ500 የሚበልጡ ኩባንያዎ በዋናነት ኢትዮጵያን አልመው በነጻ ቀጠናው ገብተው እያመረቱ ነው፡፡

ከዱባይ ወይ ማሌዝያ እንዲሁም ቻይና የሚመጣ የኢትዮጵያ ገቢ ጭነት እየቀነሰ ዛሬ መነሻው ከበረሃማዋ ጅቡቲ ሆኗል፡፡
መኪና እንዲሁም የምግብ ነክ ምርት ከነጻ ቀጠናው Made in Djibouti ተብሎ ጭምር እንደሚገባ የምንበላውን ዘይት ማየት ነው፡፡

ለቀጠናው ወሳኝ የሚባል የመርከብ ጥገና ማእከል ከሰሞኑ በይፋ ተመርቋል። Djibouti Ship Repair Yard ይባላል፡፡
ወደ ሱማሌላንድ ድንበር የሚጠጋው ዳመርጆግ ላይ ግዙፍ ሊባል የሚችል በርካታ የወደብ መሰረተልማቶችን ያካተተ ፕሮጀክት እየተሰራ ነው።

የዚህ አካል የሆነው የዳመርጆግ እጅግ ግዙፍ ነዳጅ ወደብ በቅርቡ ስራ ይጀምራል።
ከአመታት በፊት ከሸራተን በስተቀር እዚህ ግባ የሚባል ሆቴል እንዳልነበራት የሚነገረው የጅቡቲ ከተማ ዛሬ ደረጃቸው ከፍ ያለ ሆቴሎች ቁጥር እየጨመረባት ነው።
እድሜ ለወደቧ!
እድሜ ለትልቋ ገበያ ለኢትዮጵያ ትበል በጅቡቲ ሁሌ አዳዲስ እና ግዙፍ ፕሮጀክት አለ፡፡

የጅቡቲ ጥቅል ምርት/GDP የዛሬ 16 አመት 1 ቢሊየን ዶላር ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በ1990 ወደቡን መጠቀም ስትጀምር 500 ሚሊየን ብቻ።
ዛሬ 4.3 ቢሊየን ዶላር ተሻግሯል።
ከሶስት እጥፍ በላይ ተወርውሯል በ16 አመት ውስጥ።
በጅቡቲ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ የውጭ ኩባንያዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው።
የውጭ ዜጎች በብዛት መመልከት የተለመደ እየሆነ መጥቷል፡፡ ወደብ እና ባህር ከአለም ያገናኛል፡፡

የጅቡቲ እድገት አስደማሚ ነው።
ይህ በወደብ የመጣ ነው።
ወደብ ማለት የአለም አካል መሆን ማለት ነው። የአለም ህዝብ እንዲሁም እቃ ይመጣል አንተም ትሄዳለህ፣ ትመለሳለህ።
እንደ ኢትዮጵያ አይነት ትልቅ ሲሳይ ሲገኝ ደግሞ ሁኔታው ልዩ ነው።
ኢትዮጵያ ከመምጣቱዋ በፊት በጅቡቲ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዛቸውን ለመቀበል መንፈቅ ይጠብቁ እንደ ነበር ነዋሪዎችዋ ትዝታቸውን አካፍለውኛል፤ ፈረንሳይ ለጦር ሰፈር ኪራይ ስትከፍል።

ብስል ከጥሬ ሳይለዩ፣ የአገር እና ወደብ ዋጋ ሳይገባቸው ኢትዮጵያን የምታክል አገር በወጣት እድሜያቸው ለማስተዳደር ስልጣን ተቆናጠው በር ቆልፈው ላስረከቡዋት ምስጋና ይግባና ዛሬ ያ በጉጉት የሚጠበቅ የደሞዝ ወቅት ታሪክ ሆኗል በጅቡቲ።
ዛሬ የመንግስት አይደለም የግል ስራ ሰፍቷል፡፡ ገንዘብ ሁሌም አለ፡፡ ለዛውም ዶላር፡፡
ጅቡቲዎች ሃብታም እየሆኑ ነው። ጎበዞች ናቸው በተለይ ፕሬዝደንት እስማኤል ኦማር ጌሌ እድላቸውን በተገቢው ተጠቅመውበታል።

ይብላልኝ ለኤርትራ፤ ሲንጋፖር የመሆን ህልሟን በገዛ እጇ ላኮላሸችው!
ከ2002 ጀምሮ በስራ ጉዳይ ወደ ጅቡቲ ተመላልሻለው፡፡
አገር ሲያድግ፣ ሲለወጥ ምን ማለት እንደሆነ በጅቡቲ በደንብ ተረድቻለሁ።
ዘመናዊ ባቡር አስገብታለች፣ የሚጠጣ ውሃ ከኢትዮጵያ ስባለች፣ ጄኔሬተሩ ቀርቶ ከታዳሽ ሃይል ኤሌትሪክ ከኛ ትገዛለች፣ የሰለጠነ የገበያ ማእከል እና ሞል አሳይታለች።
እንደምሰማው ከዲፕሎማሲ ማእከሏ አዲስ አበባ የውጭ ዜጎች ለአስቤዛ ሸመታ ጅቡቲ ዘመናዊ ጉልት ሆናላቸዋለች።
ይህ የወደብ አገር ነው ሁሉም ይገኛል፣ ሁሉም ይመጣል በሽበሽ ነው፤ ዘመናዊ መሸጫዎቹም ተመቻችተዋል፡፡

የዲፕሎማሲ ቤተሰብ የናፈቀውን የባህር አየር እና አሸዋ ጅቡቲ መጥቶ ይቀበላል፤ ይዝናናል አዲሳባ የሌለውን ይሸምታል ወይ ሰው ገዝቶ በየጊዜው እንዲልክለት ያደርጋል፡፡
ጅቡቲ ተቀይራለች።የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል፤ ገና ትመነደጋለች!
እድሜ ለትልቋ ገበያ ኢትዮጵያ በቀጠናው መሪ የሎጅስቲክ ዘዋሪ ቦታን ይዛለች፡፡
ያርግላት እድሏ ነው፡፡

የኢትዮጵያ እድል ግን ይገርማል!
በዚህ ደሃ ኢኮኖሚ ለያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ከፍተኛ ገንዘብ ለዛውም የውጭ ምንዛሬ መክፈላችን ልብ ያደማል።
ለጅቡቲ ግን የእድገት ቁልፍ ይሆናል።
ምድር ፍርደ ገምድል ናት በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች በመቶ ሚሊየን ሰዎች እጣ ፈንታ ላይ እንዲወስኑ የሚያደርግ ታላቅ መብት ትሰጣለች፡፡
ለያንዳንዱ ሸቀጥ ዋጋ ጭማሪ፣ ለያንዳንዱ የኑሮ ውድነት ምሬት፣ በአለም መድረክ ባይተዋር ለመሆን ምክንያት፣ እንዲሁም ለስልጣኔ መዘግየት ምክንያቱ የሆኑ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች በጥላቻ እና እብሪት ተቀምጠው ወደብ ምን ያረግልናል ብለው ያሳለፉት ውሳኔ መሆኑን ሳስብ ይገርመኛል፡፡ ያሳዝነኛል!
ምድርማ ፍርደ ገምድል ናት፤
ባንተ መቸገር ሌላው ታላቅ ሲሳይ የምትቸር!

