የሰላም ፣ የፍቅር እና የትውልድ ጥሪ

ለውድ የኢትዮጵያ ህዝብ

ለተከበራችሁ የመንግስትና የፖለቲካ መሪዎች

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሀገራችን ኢትዮጵያ ያሳለፈችው የጦርነት እና የጥፋት መንገድ በህዝባችን ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ህይወት ላይ ጥልቅ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። ይህ አስቸጋሪ የታሪክ አጋጣሚ ለሁላችንም የወደፊት ጉዞ ትልቅ ትምህርት ሰጥቶናል። ጦርነት የማንንም ወገን ህመም ሳይለይ የወጣቶችን ህይወት ይቀጥፋል ፣ የቤተሰብ ምስረታን ያፈርሳል ፣ አባወራዎችን እና እማወራዎችን ያሳጣል። ያሳለፍናቸው የዕርስ በዕርስ ጦርነቶች ለዘመናት በህዝብ ሀብት የተገነቡ ትምህርት ቤቶችን ፣ ጤና ጣቢያዎችን ፣ መንገድና ድልድዮችን በቅጽበት ወደ ውድመት በመቀየራቸው ሀገርን ወደኋላ ጎትቷል። በቤታችን ፣ በጎረቤታችን ፣ በአካባቢያችን ፣ በመንደራችን ፣ በሰፈራችን ፣ በከተማችን ፣ በክልላችን ፣ በሃገራችን ሰላም ከሌለ ልማት ፣ ትምህርት ፣ ስራ እና እድገት ብሎ ነገር የማይጨበጥ ህልም ብቻ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው።

ማናቸውም የፖለቲካም ሆነ የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች በመሳሪያ ኃይል ሊፈቱ እንደማይችሉና መጨረሻቸው የማይተካ የሠውን ልጅ ህይወት ካጠፋ እና በዘመናት የተገነባ የሃገር ሃብት በደቂቃዎች ካወደሙ በኃላ እንደገና ወደ ውይይት ጠረጴዛ መምጣት እንደሆነ በተለያዩ የታሪክ ፅሁፎች ላይ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ ልዩነቶች ከመባባሳቸውና ወደ ግጭት ከመቀየራቸው በፊት በሰለጠነ መንገድ ሰከን ብሎ በመነጋገር መፍትሄ መስጠት ከሁሉ የተሻለ ቅዱስ መንገድ እንደሆነ አምናለው።

ግጭት በህዝቦች መካከል መጠራጠርና መከፋፈልን ይፈጥራል፡፡ ለዘመናት የቆየውን የማህበራዊ ትስስር ፣ የጋብቻ እና የጉርብትና እሴት ያላላል። በጦርነት ወቅት ጊዜው በወለዳቸው የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሚነዙ የጥላቻ ንግግሮች ለትውልድ የሚሻገር የስነ-ልቦና ስቃይና ቁስል ይተዋሉ ፡፡

የጦርነት ወጪዎች የሀገርን ኢኮኖሚ በማድቀቅ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ህይወት ያከብዳሉ ሚሊዮኖችን ከቀያቸው በማፈናቀል ለረሃብ ፣ ለበሽታና ለሰብአዊ እድገት መደናቀፍ ይዳርጋሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ጦርነቶችና ተፈናቃዮች ለጊዜው ተወት አድርገን ሩቅ ሳንሄድ የቅርብ ጊዜውን የሰሜን ኢትዮጵያ ግጭትና በፀጥታ ስጋት ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን አብዛኛዎቹ በአቅራቢያቸው ባሉ አዋሳኝ ከተሞችና ወረዳዎች ውስጥ ባሉ መጠለያ ካምፕ ውስጥ ያሉበትን ሁኔታ ማስታወስ በቂ ነው፡፡

በማግስቱ ቁስላችን ሳይደርቅ ወገባችን በቅጡ ሳይሽር ከጎበጥንበት ትንሽ ቀና ብለን ወደ ፊት ለማየት እየዳዳን ባለንበት ጊዜ ዛሬም በሀገራችን ኢትዮጵያ እና በትግራይ ክልል መካከል እንደገና ያንዣበበው የእርስ በእርስ የጦርነት ደመናና የስጋት ጭጋግ እጅግ ያሳስበኛል ፣ ከምንጊዜውም በላይ ያስጨንቀኛል። እኔ የዚህች ሀገር ተረካቢና የወደፊት አደራ ተሸካሚ ወጣት እንደመሆኔ መጠን አቋሜ ግልፅና የማያወላውል ነው፡፡ ከእንግዲህ በሃገሬ መሬት ላይ የደም መፍሰስና የጦርነትን አስከፊነት በኛ ዘመን ማየት በፍፁም አልፈልግም።

በዕርስ በዕርስ ጦርነት አሸናፊ የለም የሚጠፋው የጋራ ሀብታችን ፣ የሚረግፈው የወንድምና የእህቶቻችን መተኪያ የሌለው ውድ ህይወት ነው። እደግመዋለው በጦርነት ማንም አሸናፊ የለም፡፡ በሰላም ደግሞ ማንም ተሸናፊ የለም ሁሉም አሸናፊ ነው። ስለዚህ የወደፊቷን የኢትዮጵያ ትንሳኤ በመሳሪያ ውጊያ ሳይሆን በሰላም ፣ በፍቅር ፣ በይቅርታና በልማት ከመንግስታችን ጎን በመሆን ታሪክ ለመፃፍ ወስኜ ተነስቻለሁ፡፡

ሃገርን እየመራህ ያለህ መንግስት ሆይ እስከዛሬ የሄዳችሁበትን የሰላም ጥረት እና ድርድር እንደ አንድ ሀገሩን እንደሚወድ አደራ ተቀባይ ወጣት እያመሰገንኩ አሁን ግን ለአዲሱ ትውልድ አንድ የመጨረሻ ዕድል እንድትሰጡኝ ለሃገራቸው ነፃነትና ክብር ሲሉ በሃገሬ መሬት ላይ ከፊትና ከጀርባ ተመተው መስዋዕት በሆኑላት ጀግና ልጆቿ ስም እጠይቃለሁ። ጥሪዬ ቀላል ግን ጥልቅ ነው።

የመጀመሪያ ጥሪዬ የመሳሪያ ድምፅ ጠፍቶ የሰላም አየር እንዲነፍስና በወንድማማቾች መካከል የሚደረግ ማንኛውም ውጊያ በቃ ሊባል ይገባል የሚል ሲሆን ሁለተኛው ጥሪዬ የጦር ልብስና መሳሪያ አንግቤ ሳይሆን የሰላም ፣ የንፅህና እና የእርቅ ምልክት የሆነውን ነጭ የኢትዮጵያ የባህል ልብስ ለብሼ በሀገራችን በሚገጣጠሙት የኤሌክትሪክ መኪኖች ተሳፍሬ ወደ ወንድሞቼና እህቶቼ ወደ ትግራይ ክልል እንድጓዝ እንዲፈቀድልኝ፡፡ እንዲሁም ሶስተኛው ጥሪዬ በትግራይ ክልል የጥፋትና የደም ጠባሳ ባረፈባቸው ቦታዎች ላይ የወንድማማችነት እና የይቅርታ ምልክት እንዲሆን በጥይት ፋንታ የህይወት ችግኝ በመትከል የቆሰሉ ልቦችን በጥበብና በፍቅር ፈውሼ ዘላቂ ሰላምን አስፍኜ ለመመለስ አዲስ ተስፋን ሰንቄአለሁ።

የተከበራችሁ የሀገራችን መሪዎችና አመራሮች ውጊያ ሰላምን አያመጣም ይቅርታና ውይይት ግን የተሰበረውን አክሞ አዲስ ሰው ያደርጋል፡፡ አሁን ያለንበት ወቅት ኢትዮጵያ እየመከረች ባለበት ጊዜ በመሆኑ እኔ ሀገር ተረካቢ ወጣት የሰላም አምባሳደር ሆኜ በኢትዮጵያና በትግራይ መካከል ያለውን የሰይጣን ግንብ በፍቅር ማፍረስ እፈልጋለሁ። በተለያዩ ስርዓቶች ምክንያት ተወልደን ባደግንበት ሃገር ላይ ያሳለፍነው መራር መንገድ ለወደፊቱ ትውልድ የሚሆን ትልቅ ማስጠንቀቂያና የህይወት ትምህርት ስለሆነ ሰላምን መጠበቅና ማጽናት የሁላችንም የዘወትር ኃላፊነት በመሆኑ ይህን የሰላም ጉዞ እንድጀምርና ታሪክ የሚዘክረውን መንግስታችንም የሚደግፈውን አዲስ ምዕራፍ እንድፅፍ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ፍቃዶትና ድጋፎት አይለየኝ።

ይቅርታ ፣ ምህረት እና ፍቅር ሞትን ድል ይነሳል !

ወጣት ሃይማኖት ደመቀ

ማስታወሻ:- ከላይ የቀረበው ሀሳብ ሙሉ በሙሉ የጸሀፊው ነው።

Related

የወደብ ባለቤትነት ምንነት

ሙሉቀን የወንድወሰን (ነፃ ሃሳብ) ለኢኮኖሚ ወደብ ምን ማለት እንደሆነ እንዲገባህ...

የውርስ ክርክር እና ቅሌት!

ሺ ብታረጅ ልጅ ያቦካው የሚባለው ተረት በድሜ ለገፋም ልጅ...

Popular Categories