በመካከለኛው ምስራቅ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ ቁልፍ የሆነው የሆርሙዝ የባህር ሰርጡ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መዘጋቱን ተከትሎ፣ ኢራቅ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በፋርስ ባህረ ሰላጤ ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ አማራጭ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧዎችን በፍጥነት ለመዘርጋት እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ተገለጠ።
ኩንትኪዩብ ቴክኖሎጂ የተባለው የኢኮኖሚ መረጃ ተቋም ይፋ ያደረገው አዲስ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከጦርነቱ መነሳት በኋላ በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ በሆርሙዝ ላይ ብቻ ጥገኝነቷ የበረታው የኢራቅ የወጪ ንግድ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ደርቋል።
ሀገሪቱ ከጦርነቱ በፊት በቀን 93 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ በዚሁ መተላለፊያ በኩል ትልክ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር የላከችው ግን 10 ሚሊዮን በርሜል ብቻ መሆኑ ተመልክቷል። ይህም 53 በመቶ የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርቷ (GDP) በነዳጅ ላይ ለተመሰረተው የኢራቅ ኢኮኖሚ ከባድ መናጋትን ፈጥሯል።
ይህን ቀውስ ለመቋቋም የኢራቅ ካቢኔ በኩርዲስታን በኩል አድርጎ ወደ ቱርኳ የሜዲትራኒያን ወደብ ጄይሃን (Ceyhan) የሚዘልቀውን የነዳጅ ቧንቧ መስመር በከፍተኛ ፍጥነት ስራ ላይ ለማዋል ወስኗል።
ይህም አሁን ያለውን የቀን 220,000 በርሜል የመላክ አቅም ወደ 770,000 በርሜል እንደሚያሳድገው ይጠበቃል።
በሌላ በኩል የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (አቡ ዳቢ) የሆርሙዝ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ በመተው ነዳጇን በቀጥታ ወደ ፉጃይራ ወደብ የሚያደርሰውን አዲስ “የምዕራብ-ምስራቅ” የነዳጅ ቧንቧ ዝርጋታ እያፋጠነች ትገኛለች።
እ.ኤ.አ. በ2027 ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት የሀገሪቱን ብሄራዊ የነዳጅ ኩባንያ (ADNOC) አቅም በእጥፍ ያሳድገዋል ተብሏል።
ይሁን እንጂ የኤምሬትስ የፉጃይራ ተርሚናልም ሆነ የሳውዲ አረቢያ “የምስራቅ-ምዕራብ” የነዳጅ ቧንቧ መስመር በቅርቡ የድሮንና የሌሎች ጥቃቶች ሰለባ መሆናቸው የአማራጭ መስመሮችን ደህንነት አሳሳቢ አድርጎታል።
ከዚህም በላይ አሁን ያሉት አማራጭ መስመሮች በሙሉ ተዳምረው እንኳን ከጦርነቱ በፊት በሆርሙዝ በኩል ያልፍ የነበረውን የቀን 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ መተካት እንደማይችሉ የዓለም አቀፉ የኢነርጂ ኤጀንሲ መረጃ ያሳያል።
በአሁኑ ወቅት በሆርሙዝ በኩል የሚያልፉ መርከቦች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰ ሲሆን፣ በባህረ ሰላጤው ውስጥ የተዘጋጉ መርከቦች የቴህራንን ይሁንታ ካላገኙ የኢራን ኃይሎች ጥቃት ሊሰነዝሩባቸው እንደሚችል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከኢራን ጋር ከተባበሩ የአሜሪካ ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል የሎይድስ ሊስት የባህር ትራንስፖርት መረጃ አመልክቷል።@seco


