ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የቀጣይ ትውልድ ተስፋ መሆናቸውን ቀጥለዋል
ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ኦሀዮ ግዛት ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ባለትዳር እና የተዋጣላቸው ኢንቨስተሮች ለማ ጌታቸው እና ዶ/ር ገነት እንዳለ መጪውን ትውልድ የማብቃት ስራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ፡፡

መጪው ትውልድ ጥራቱን የጠበቀ አገር ተረካቢ እንዲሆን ባለፉት አመታት የበኩላቸውን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን ጠቅሰው ይህን ትውልድን የማነጽ ተግባራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያስታወቁት፡፡
ከዚሁ መልካም ተግባራቸው ጋር ተያይዞ የትዳር አጋሮቹ ለማ እና የምህንድስና ሊቋ ዶ/ር ገነት ለበጎ ተግባራቸው በመሰረቱት ለማ እና ዶክተር ገነት ፋውንዴሽን/ Lemma and Dr Guenet Foundation አማካኝነት በዘመናዊ መልክ ያስገነቧቸውን ዲጂታል ላይብረሪዎች አስመርቀዋል፡፡

በሀረር ከተማ በሚገኙ ት/ቤቶች ያስገነቧቸው ሁለት ላይብረሪዎች ማክሰኞ ሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓም በተረቁበት ወቅት በተወካያቸው አማካኘነት እንደተገለፀው ቀደም ሲል ሁለቱ አገር ወዳድ ጥንዶች ምንም እንኳን መኖሪያቸውን በርቀት ቢቀልሱም በአገራቸው በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራትን አከናውነዋል፡፡
ለዚህም የተለያዩ እውቅናዎችን ማግኘት የቻሉ ሲሆን፤ ይህ መልካም ተግበራቸው መሰረቱ ጠንክሮ እንዲራመድ እና የተሻለ ውጤት ማምጣት እንዲችል ከጥቂት አመታት ወዲህ ባቋቋሙት ፋውንዴሽን ድጋፎችን በተለያየ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተቀናጀ መልኩ እያደረጉ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የፍውንዴሽኑ የፕሮጀክት እና ስትራቴጂካል እቅድ አማካሪ እንዲሁም የአጋሮቹ ተወካይ አቶ ኤድመን ተስፋዬ በላይበራሪ ምረቃው ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያን ለመቀየር እና እድገቷን ለማረጋገጥ መሰረቱ ላይ መስራት ነው ብለው የሚያምኑት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የኢንጂነሪንግ ክፍል ቀዳሚ ከሆኑት ሴት መምህራን አንዷ የነበረችው ዶ/ር ገነት እና የተዋጧለት የፈርማሲ ባለሞያ እና ስራ ፈጧሪ ባለቤቷ ለማ በመማር ማስተማር እንዲሁም ተማሪ ተኮር ድጋፎች ላይ ለበርካታ አመታት አመርቂ ተግባራትን ነው የፈፀሙት፡፡

ዘንድሮም ፋውንዴሽኑ በሀረር ከተማ በሚገኘው ሀረር ሁለተኛ ደረጃ (ጁኔር) እና የራስ መኮንን መለስተኛ ትምህርት ቤቶች በዘመናዊ መልክ ያሰሯቸውን ዲጂታል ላይበራሪዎች የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ሃላፊዎች እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓም አስመርቀዋል፡፡
በሐረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ የትምህርት ቤቶች ጥራትና መሻሻል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክር የሆኑትና በምረቃ ስነስርአቱ ላይ የተገኙት አቶ ጃፋር መሀመድ ዛሬ ፋውዴሽኑ ያደረገው ድጋፍ ለትውልድ ከማሰብና አሻራን ከማስቀመጥ ባሻገር የሰብአዊነት ማሳያ ነው ብለዋል።

ለዚህ ቀና የሆነ ሰብአዊ ተግባር ቢሮአችን ከልብ ያመሠግናችኋል ያሉት የቢሮው ሃላፊ የተደረገው በጎ ተግባር የትምህርት ግብአትቶችን እጥረት የቀረፈ እና ለትምህርት ጥራት ከፍተኛ አስተዋጾ ያበረከተ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
“ድጋፋችን መጪውን ትውልድ መቀየር ነው፣” በማለት መርሃቸውን የሚገልጹት አቶ ለማ በተጠቀሱት ሁለት ትምህርት ቤቶች ባለፉት አመታት በርካታ ድጋፎች ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ በቅርብ አመታት ተማሪዎቹ እያስመዘገቡት ላለው የላቀ ውጤት የኛ ድጋፍ አስተዋጽኦ እንዳለው እንረዳለን ብለዋል፡፡

ቀጣይ እቅድ
በቢዝነሱ አለም በሰሜን አሜሪካ የተዋጣላቸው የሪል ስቴት አልሚ መሆን የቻሉት ሁለቱ ጥንዶች አምናም በተመሳሳይ በምስራቅ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በንፁህ ውሃ፣ መፃዳጃ፣ የትህምርት መርጃ እና ተያያዥ ድጋፎችን ያደረጉ ሲሆን፡፡
በቀጣይ ፋውንዴሽኑ አድማሱን አስፍቶ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለየይ ለተማሪዎች ምቹ የመማሪያ ድባብ በመፍጠር እና አጋዥ የትምህርት መሳሪየዎችን በማመቻቸት ላይ ያተኮረ ድጋፍ በማቅረብ እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት፡፡

በሐረር በተመረቁት ዘመናዊ ዲጅታል ላይብረሪዎች ከ ስድስት ሺህ በላይ መፅሀፍት የተሰባሰቡ ሲሆን ተማሪዎች አጋዥ መፃህፍትን ያለ ውጣ ውረድ ማግኘት የሚችሉ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ፋውንዴሽኑ ቀደም ሲል በሁለቱ ትምህርት ቤቶች ከ 85 ያላነሰ ኮምፒውተሮችን በመለገስ ተማሪዎች ለመማር ማስተማር ሂደት እንዲጠቀሙበት እንዲሁም አገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተናዎችን መፈተን እንዲችሉ ማድረግ ያስቻለ ነው፡፡

በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም በሀረር ራስ መኮንን እና ሆህተ ምስራቅ አዳሪ ትምህርት ቤት የንጽሁ መጠጥ ውሃ ቁፍሮና የመጸዳጃ ቤት ያስገነባው ዶ/ር ገነት እና አቶ ለማ ያቋቋሙት ፋውንዴሽን በተጨማሪም በሀረር ሸንኮር ወረዳ ከሀምሳ በላይ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ያደረገ መጸዳጃ ቤት ገንብቶ አስረክቧል።
ፍውንዴሽኑ ማክሰኞ ካስመረቃቸው ዘመናዊ ዲጅታል ላይበራሪዎች በተጨማሪ በሀረር ከተማ ለሚገኙ ከሁለት መቶ በላይ ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ማቅረቡ ነው የተገለጸው፡፡

ፍውንዴሽኑ በቀጣይም በሐረር ከተማ በትምህርቱ ዘርፍና በንጹህ መጠጥና የመጸዳጃ ቤት ግንባታዎች ላይ በመሳተፍ ሀገራዊ ግዴታውን እንደሚወጣ ነዋሪነታቸው በአውሮፓ ያደረጉት የፍውንዴሽኑ የፕሮጀክትና ስትራቴጂካል እቅድ አማካሪ የአጋሮቹ ተወካይ አቶ ኤድመን ተስፋዬ በምርቃቱ ስነስርአት ላይ ገልጸዋል።

አቶ ኤድመን አክለውም የአቶ ለማ ጌታቸው እና ዶ/ር ገነት እንዳን አርአያ በመከተል በውጪ የሚኖሩ የሀረር ልጆች የተማሩበትን ትምህርት ቤትና የወጡበትን ማህበረሰብ ችግር የሚቀርፍ ተግባር ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።



