በባንኮች የውጭ ምንዛሬ አመዳደብ ላይ ደንበኞች ቅሬታ እያቀረቡ ነው

ብሔራዊ ባንክ ከውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ጋር ከባንኮች መሻሻል እንደሚጠብቅ ገልጾ የቁጥጥር ስራ መጀመሩን አስታውቋል

የውጭ ምንዛሬ ገቢ እየጨመረ ቢሆንም ለገበያው በተገቢው መንገድ እየቀረበ አደለም ሲሉ ደንበኞች እና የባንክ ባለሞያዎች ቅሬታቸው ለETBusinessView ገለጹ፡፡ በቂ የውጭ ምንዛሬ በህጋዊ ገበያ በበቂ ሁኔታ ስለማይቀርብ የውጭ ተጓዦች ሳይቀር አሁንም ወደ ጥቁር ገበያ እንዲያመሩ በመገደዳቸው በባንኮች የምንዛሬ አመዳደብ ላይ ጥያቄ አስነስቷል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሬን ለደንበኞቻቸው በሚያከፋፍሉበት እና በሚያስተዳድሩበት አሠራር ላይ ቁጥጥሩን ለማጠናከር መወሰኑን አስታውቋል።

የባንኮች የውጭ ምንዛሬ አመዳደብ አሠራር እና የደንበኞች አያያዝ ከባንኩ የቁጥጥር ሥራዎች አንዱ እንደሆን የማእከላዊ ባንኩ ገዢ አቶ ኢዮብ ተካልኝ (ፒኤችዲ) ገልጸዋል።

ስለጉዳዩ የሚያውቁ የባንክ ባለሞያዎች ለ ETBusinessView  እንደተናገሩት ባንኮች ለደንበኞች የውጭ ምንዛሬ እንዲያቀርቡ  ብሄራዊ ባንክ ግፊት እያደረገ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ብሔራዊ ባንኩ ባንኮች የውጭ ምንዛሬን ለደንበኞች እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ጫና እያደረገ ቢሆንም፣ በባንኮች ዘንድ ያለው የምንዛሬ አቅርቦትና የአመዳደብ አሠራር አሁንም በበርካታ ደንበኞች ዘንድ ቅሬታ እሚፈጥር መሆኑን ከባንክ ዘርፉ ጋር የተያያዙ ባለሙያዎች ለETBusinessView ገልጸዋል።

በተለይም ለጉዞ፣ ለትናንሽ ግዢዎችና ለሌሎች ሕጋዊ ፍላጎቶች አነስተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚፈልጉ ግለሰቦች ከባንኮች በቂ አቅርቦት ማግኘት እንዳልቻሉ ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ። ከሁለት ዓመት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነጻጸርም በደንበኞች የምንዛሬ ተደራሽነት ረገድ አርኪ የሚያሰኝ ለውጥ እንዳልተመዘገበ ባለሞያዎች ያስረዳሉ።

በሐምሌ 2016 የተጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የውጭ ምንዛሬ ገበያው በገበያ መር አሠራር እንዲመራ አቅጣጫ በመያዙ ከወጪ ንግድ ባሻገር በተለያዩ መንገዶች የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ መጨመሩ የባንኮችን የምንዛሬ ማግኛ አቅም እንዳሳደገ ባለሙያዎቹ ያመለክታሉ።

ሆኖም የውጭ ምንዛሬ ገቢ መጨመሩ በገበያው ላይ የሚታይ ተመጣጣኝ አቅርቦትና ለሕዝብ የተሻለ ተደራሽነት ሊፈጥር እንዳልቻለ ይናገራሉ። በዚህም ምክንያት ከባንኮች የሚፈልጉትን ምንዛሬ ማግኘት ያልቻሉ ግለሰቦችና ነጋዴዎች ወደ ጥቁር ገበያው እንዲያመሩ እየተገደዱ ነው።

ባለሙያዎቹ የችግሩ መንስኤ የምንዛሬ እጥረት ብቻ ሳይሆን በባንኮች የሚታየው የአመዳደብ አሠራር፣ የአገልግሎት መጓተትና የግብይት ወጪ መጨመርም እንደሆኑ ያስረዳሉ።

ይህ ጉዳይ በህጋዊ  እና ትይዩ ገበያው መካከል ላለው የሰፋ ልዩነት አለመጥበብ አይነተኛ ምክንያ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህ ጥሩ ማሳያ ባለፈው የካቲት ወር በባህረ ሰላጤው የተነሳውን ቀውስ ተከትሎ በርካታ የሻንጣ ነጋዴዎች ወደ ዱባይ መጓዝ በማቆማቸው የትይዩ ገበያው ዋጋ በከፍተኛ መጠን መቀነሱ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡

ባለሙያዎቹ ይህ ሁኔታ ግለሰቦች ከባንኮች በቂ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት እንደማይችሉ ጥሩ አመላካች ነው ሲሉ ገልፀው፤ በብሔራዊ ባንክ በኩል በጨረታ የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬም በገበያው ላይ የሚጠበቀውን ለውጥ እንዳላስገኘ ይናገራሉ።

ምክንያቱም ባንኮች በጨረታ የሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ድርሻ የቀድሞ የክፍያ ውዝፎችን ለመክፈል እንደሚውል ነው የሚጠቅሱት፡፡

“ባንኮች በጨረታ ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ አብዛኛው የቀድሞ የክፍያ ውዝፎችን ለመፍታት ይውላል። በዚህ ምክንያት ብሔራዊ ባንክ ለገበያው ከፍተኛ መጠን ያለውን ምንዛሬ ቢያቀርብም በገበያው ላይ የሚታይ መረጋጋት አይፈጠርም፣” ሲሉ አንድ ባለሙያ ገልጸዋል።

በተጨማሪም አንዳንድ ግለሰቦች በተለያዩ ባንኮች በኩል የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ሲችሉ፣ ተራ ደንበኞችና ተጓዦች ግን አነስተኛ መጠን እንኳን ማግኘት እንደሚቸገሩ ይጠቁማሉ።

“የነጻ ገበያ መርህ ማለት ለጥቂት ግለሰቦች ከፍተኛ መጠን ያለውን ምንዛሬ በመስጠት ለብዙኃኑ ግን የተገደበ አቅርቦት ማድረግ አይደለም፣” ሲሉ ነው ባለሙያዎቹ የሚከራከሩት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ባንኮች በውጭ ምንዛሬ ግብይት ላይ የሚጥሏቸው ኮሚሽኖችና ሌሎች ክፍያዎች የመደበኛውን ገበያ ወጪ ከፍ በማድረግ በጥቁር ገበያው ያለውን የዋጋ ልዩነት እንዲቀጥል እያደረጉ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ያምናሉ።

ኢዮብ (ፒኤችዲ) ማክሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ብሔራዊ ባንኩ በባንኮች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር ከመደበኛ የብድር ጥራትና የካፒታል በቂነት (adequacy) መለኪያዎች ባሻገር ወደ ውጭ ምንዛሬ አስተዳደርና አመዳደብ እንደሚያስፋፋ ተናግረዋል።

ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ጥያቄዎችን እንዴት እያስተናገዱ እንደሆነና ለደንበኞች የሚያደርጉት አመዳደብ ምን ያህል ፍትሐዊና ተደራሽ እንደሆነ በቅርበት እንደሚገመገምም አመልክተዋል።

ብሔራዊ ባንኩ በተለይ ከየካቲት አንስቶ በርካታ ማሻሻያዎችን ከውጭ ምንዛሬ ግብይት አስተዳደር ጋር እያደረገ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

በማሻሻያዎቹ የአገልግሎት ላኪዎች እና ባንኮች የምንዛሬ ግኝት ክፍፍል ግዴታ ሙሉ ለሙሉ ተወግዷል፤ ለቤተሰብ ጉዳይ እስከ 3,000 ዶላር የውጭ ምንዛሬ ያለ ውጣ ውረድ መፍቀድ እንዲሁም እስከ 20,000 ዶላር ቅድመ ክፍያ እንዲፈጸም ተፈቅዷል።

በተጨማሪም ባንኮች የብሔራዊ ባንክን ቅድመ ፈቃድ ሳያስፈልጋቸው የወደፊት የምንዛሬ ግብይቶችን (Forward Transactions) እንዲያከናውኑ ተፈቅዷል። ከዚህ ባሻገር የውጭ ሀገር ኢንቨስትመንት ጥያቄዎችን በየጉዳዩ እየተመለከተ የመፍቀድ ሥልጣንም ለብሔራዊ ባንክ ተሰጥቷል።

በተመሳሳይ የሸቀጦች ላኪዎች ለባንኮች ማስረከብ የሚጠበቅባቸው የውጭ ምንዛሬ መጠን ወደ 30 በመቶ እንዲቀንስ የተወሰነ ሲሆን፣ የቀረውን መጠን ላኪዎች በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ተፈቅዷል።

ይሁን እንጂ የዓለም አቀፍ አጋሮች የውጭ ምንዛሬ ገበያውን ለማረጋጋት የፖሊሲ ማሻሻያዎች ብቻቸውን በቂ ላይሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። በዚህም ተጨማሪ ለውጥ መደረግ እንዳለበት ነው የሚመለክቱት፡፡

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ተመረቀ

“ከማገዳችን በፊት ከአምስቴ በላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል!” የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ያስመረቀው...

Popular Categories