የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በቂ የሥራ ዕድል እየፈጠረ አለመሆኑ ተገለፀ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ይፋ ባደረገው አዲስ የማክሮ ኢኮኖሚ ትንበያ ሪፖርት፣ ሀገሪቱ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት ተስፋ ቢኖራትም ዕድገቱ በቂ የሥራ ዕድል እየፈጠረ አለመሆኑንና የዋጋ ግሽበትም እስከ 2030 (እ.ኤ.አ) ከ14 በመቶ በላይ ሆኖ ሊቀጥል እንደሚችል አስታውቋል።

«የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምና ትንበያ» በሚል ርዕስ የወጣው ይህ ሪፖርት፣ ባለፉት 25 ዓመታት (ከ2000 እስከ 2025) በሀገሪቱ የተመዘገበው የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ትስስር ደካማ ሆኖ መቆየቱን ያሳያል። ጥናቱ እንደሚያመለክተው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት በ1 በመቶ ሲያድግ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራው ያደገው በ0.27 በመቶ ብቻ ነው።

ሪፖርቱ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅሙ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል ከፍተኛ ልዩነት አሳይቷል። በዚህም መሠረት የአገልግሎት ዘርፍ 0.51 በማስመዝገብ ቀዳሚውን ሥፍራ ሲይዝ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ 0.28፣ እንዲሁም የግብርና ዘርፍ 0.04 ብቻ አስመዝግበዋል።

ይህ ውጤት ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪን ለማስፋፋትና መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የምታደርገው ጥረት ምን ያህል ለዜጎች ተጨባጭ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ነው የሚለውን ጥያቄ አጭሯል።

ሪፖርቱ አክሎም፣ የሥራ ዕድል ዕድገቱ በዋናነት በነባር ዘርፎች መስፋፋት የመጣ እንጂ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ያበረከተው አስተዋጽኦ አነስተኛ መሆኑን ገልጿል። ግብርና ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ እየቀነሰ ቢመጣም አሁንም ከፍተኛውን የሰው ኃይል ቀጥሮ ይዟል። በአንጻሩ የኢንዱስትሪው ዘርፍ ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው ምርት እያደገ ቢሆንም፣ ከዕድገቱ ጋር የሚመጣጠን የሥራ ዕድል መፍጠር አልቻለም።

በሌላ በኩል አዲሱ ጥናት የዋጋ ግሽበት ጫና አሁንም አሳሳቢ ሆኖ እንደሚቀጥል ተንብዮአል። በመደበኛው ትንበያ መሠረት አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በ2026 ወደ 16.5 በመቶ ከፍ ካለ በኋላ፣ በ2030 ቀስ በቀስ ወደ 14.9 በመቶ ዝቅ ይላል ተብሎ ይጠበቃል።

ሆኖም የገንዘብ አቅርቦት መስፋፋትን በጥብቅ መቆጣጠር ከተቻለ፣ በ2030 የዋጋ ግሽበቱን ወደ 9.2 በመቶ ማውረድ የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ጥናቱ ጠቁሟል። ጥናቱ እንዳመለከተው የገንዘብ አቅርቦት በ1 በመቶ ሲጨምር አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት በ1.55 በመቶ ነጥብ ይጨምራል።

ከነዚህ ግኝቶች በመነሳት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር፣ ብዙ የሰው ኃይል የሚጠቀሙ የኢንዱስትሪ ልማቶች እንዲበረታቱ፣ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር እንዲፋጠን እና የገንዘብ አቅርቦት ቁጥጥር እንዲጠናከር የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን አቅርቧል።

ሪፖርቱ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በየዓመቱ ከ9 በመቶ በላይ እንደሚያድግ ቢተነብይም፣ ይህንን ዕድገት ወደ ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የዜጎችን የመግዛት አቅም ወደ ማሻሻል መቀየር ትልቅ የቤት ሥራ መሆኑን አመልክቷል።SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ተመረቀ

“ከማገዳችን በፊት ከአምስቴ በላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል!” የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ያስመረቀው...

Popular Categories