የሱዳን ጉዳት የኢትዮጵያ ጉዳት ነው … ከማንም ሳንወግን እናደራድራለን ብለዋል!!
ሱዳን በአሁኑ ወቅት ቀድሞ ወዳጅ በነበሩ ሁለት ጀነራሎች የሃሳብ ልዩነት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከገባች አራት ዓመት አስቆጥራለች፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ ያቀረቡትም ይህ ከዜጎቿ አልፎ ለቀጠናው አሳሳቢ የሆነውን የእርስ በእርስ ጦርነት መፍትሄ ለመፈለግ ኢትዮጵያ ዝግጁ ናት የሚል ነው፡፡
ጀነራል አብድልፈታህ አል ቡርሃን የሱዳን ጦርን ይዘው ካርቱምንና አብዛኛውን ምስራቅ ሱዳን እያስተዳደሩ፣ ጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ ሄሚቲ ደግሞ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይልን እየመሩ ዳርፉርንና አብዛኛው ምዕራብ ሱዳንን እያስተዳደሩ ግዛታቸውንና ተፅእኖአቸውን ለማጠናከር የእርስ በእስር ውጊያ ላይ ካሉ አራት ዓመታት አልፈዋል፡፡
በርካታ የድርድር ሙከራዎች ቢኖሩም ቀድሞ በየመን ዘመቻ እና ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽርን በማስወገድ “ወንድማማች” ነን ሲባባሉ የነበሩትን ጀነራሎች የሚያቀራርብ አልተገኘም፡፡

የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከሁለቱ ተቃራኒ ወገኖች ባለፈ በርካታ ወገኖች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ በዛው በሱዳን የታጠቁ ሃይሎች እንዲሁም ግብፅን ጨምሮ ጎረቤት ሃገራት እና የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጣልቃ መግባታቸው ለሰላም በሩ እንዳይከፈት አድርጓል የሚሉ ትንታኔዎች አሉ፡፡
አሁን የአደራዳሪነት ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የአልበሽር መንግስት መውደቁን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2019 የሱዳን የሽግግር ምክር ቤት እንዲመሠረትና የተለያዩ ሃይሎች እንዲግባቡ በማድረግ መልካም ዝና አላቸው፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ እንደ ሌሎቹ የጎረቤት ሃገራት ሁሉ አንዱን የሱዳን ሃይል በመደገፍ እያዳላች ነው፣ ከተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ጋር ያላትን ቅርበት መነሻ በማድረግ በተለይም ለፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ ድጋፍ ትሰጣለች የሚሉ አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ ታደራድራችሁ በሚለው ጥያቄያቸው የገለልተኝነት ጥያቄ በሃገራቸው ላይ እንደማይነሳ አስረግጠው፣ ወንድም የሆነው የሱዳን ህዝብ ስቃይ ስቃያችን ከዛም አልፎ የሱዳን ቀውስ እና ስጋት እንደተጎራባች ለኛም ቀጥታ ስጋት ነው ብለዋል በዓረብኛ ባስተላለፉት ጥሪ፡፡
የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት በሺዎች ኪሎሜትር ለምትዋሰነው ኢትዮጵያ ቀጥተኛ የፀጥታ ስጋት የደቀነ ሲሆን በተለይም በቤኒሻንጉል እና አማራ ክልሎች እንዲሁም ከኤርትራ ጋር በሚያስኑ አካባቢዎች ኢትዮጵያን የሚያጠቁ የህወሃት እና ሌሎች ሃይሎች መሳተፋቸውን ለመንግስት ቅርብ የሆኑ ምንጮች ሲጠቅሱ ቆይተዋል፡፡
የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ከሞት ባለፈ ከተሞችን እያመሳቀለና ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ እያስከተለ ሲሆን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጥሪ በቀጣይ ከዋነኞቹ የሱዳን ተፋላሚ ሃይሎች የሚሰጠው ምላሽ ይጠበቃል፡፡SECCO


