የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዳዲስ ፈቃድ ያገኙ የመልቲሞዳል ትራንስፖርት ኦፕሬተሮችን ከባንክ ሥርዓት ጋር ለማቀናጀት አዲስ እንቅስቃሴ ጀመረ። ባንኩ በምስረታ ላይ ላሉት አዳዲስ ኦፕሬተሮች የብድር መተማመኛ ሰነድ (ኤልሲ) ግብይት ፈቃድ ለመስጠት እንዲያስችለው፣ የሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ፈቃድ ያገኙ ተቋማትን ዝርዝር በይፋ እንዲያቀርብለት ጠይቋል።
እስካሁን ድረስ በመልቲሞዳል የጭነት ሥራዎች ላይ ከባንክ ሥርዓት ጋር እንዲሠራ ፈቃድ ከተሰጠው መንግሥታዊ ተቋም ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ (ኢባትሎ) ውጭ ሌላ አካል ሰፊ ተሳትፎ አልነበረውም። የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን መጀመሪያ ላይ ሦስት የግል ኦፕሬተሮችን ፈቃድ የሰጠ ሲሆን፣ በቀጣይም በ2025 መጀመሪያ ላይ ለሌሎች ሦስት ኩባንያዎች ተጨማሪ ፈቃድ ሰጥቷል። ይሁን እንጂ ኦፕሬተሮቹ የንግድ ፈቃድ ቢያገኙም፣ የክፍያ ሰነዶቻቸው በባንክ ሥርዓት ውስጥ እውቅና ባለማግኘታቸው ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ለመጀመር ሳይችሉ ቆይተዋል።
በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ የባህር ላይ ጭነት ደረሰኝ ሰነድ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፤ ለጭነት ማረጋገጫ፣ የትራንስፖርት ውል ማሳያ እና አስፈላጊ ሲሆንም የባለቤትነት ማረጋገጫ ሆኖ ያገለግላል። የዚህ ሰነድ እውቅና ማግኘት ኦፕሬተሮች ዓለም አቀፍ ጭነቶችን ለመቆጣጠር እና የውጭ ንግድ ክፍያዎችን በባንክ በኩል ለማከናወን እጅግ ወሳኝ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ማዕከላዊ ባንክ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማኅበር ያቀረበውን ጥያቄ በመቀበል የገላን ሁለገብ ወደብ ለኤልሲ ግብይት ብቁ መዳረሻ ሆኖ እንዲታወቅ ፈቃድ ሰጥቷል። ይህ ውሳኔ አስመጪዎች አዲሱን ተቋም ሙሉ በሙሉ እንዳይጠቀሙበት እንቅፋት ሆኖ የቆየውን ትልቅ የቁጥጥር ፈተና ያስቀራል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማኅበር የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማስፋት “ግሎባል ሎጂስቲክስ” የተሰኘ የሎጂስቲክስ ክፍል አቋቁሞ፣ ገቢ ሸቀጦችን ለመቆጣጠር የሚያስችል የገላን ወደብን ጨምሮ ተያያዥ መሠረተ ልማቶችን ገንብቷል።
በዚህም መሠረት የባቡር ድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ታከለ ኡማ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ ማኅበሩ ያስገነባው የገላን ወደብ ለኤልሲ ግብይት በይፋ እንዲመዘገብላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር።
በኅዳር ወር ላይ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ኦፕሬሽን እና ሪዘርቭ ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የተፈረመ ደብዳቤ ለንግድ ባንክ እና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተላልፏል። በደብዳቤውም የገላን ወደብ በኤሌክትሮኒክስ ባለ አንድ መስኮት ሥርዓት ሙሉ በሙሉ እስኪቀላቀል ድረስ፣ ለጊዜው ግብይቶቹ በንግድ ባንክ በኩል በወረቀት (በእጅ) እንዲከናወኑ አዟል።
ፍቃድ አግኝተዋል ከተባሉት ስድስት ኩባንያዎች መካከል ገልፍ ኢንጎት፣ ፓናፍሪክ ግሎባል፣ ጥቁር አባይ እና ኮስሞስ ይገኙበታል። የማዕከላዊ ባንክ ይህ ውሳኔ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እና ሥራ ለመጀመር ሲጠባበቁ የነበሩ ኦፕሬተሮች በደስታ ተቀብለዉታል። የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ የኢትዮጵያ ሎጂስቲክስ ዘርፍ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ለዋጋ ንረት መንስኤ ሆኖ የቆየ በመሆኑ፣ አሁን የተወሰዱት እርምጃዎች የሀገሪቱን የኤክስፖርት ተወዳዳሪነት ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው።SECO


