አፍሪካ ግማሽ ያህሉ የግጦሽ መሬቶች ከመሸከም አቅማቸው በላይ ለግጦሽ እየዋሉ መሆኑ ተገለጸ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. 2026 “ዓለም አቀፍ የግጦሽ መሬቶችና አርብቶ አደሮች ዓመት” ተብሎ እንዲከበር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅት፣ በአፍሪካ አህጉር ግማሽ ያህሉ የግጦሽ መሬቶች ከአቅም በላይ ለሆነ ግጦሽ መጋለጣቸውን አንድ አዲስ ሳይንሳዊ ጥናት አስጠነቀቀ።

በ “ኔቸር ኮሙኒኬሽን” መጽሔት ላይ የታተመው ይህ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ ከአህጉሪቱ 49 ሀገራት መካከል የ25ቱ ሀገራት የግጦሽ መሬቶች ሥነ-ምህዳራዊ የመሸከም አቅማቸው በላይ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው።

ይህ አሳሳቢ ሁኔታ በተለይ በሰሜናዊ የአፍሪካ ክፍሎችና በምስራቅ አፍሪካ የሚገኙትን ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳንን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚነካ ተጠቁሟል።

የጥናቱ ግኝቶች እንደሚያሳዩት፣ ምንም እንኳን የአፍሪካ የግጦሽ መሬቶች የሚያመነጩት ዕፅዋት ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት አንጻር መጠነኛ ጭማሪ ቢያሳይም፣ የአህጉሪቱ የከብት ቁጥር ግን ከዚያ በበለጠ ፍጥነት አድጓል።

 እ.ኤ.አ. በ2020 አፍሪካ የነበራት የከብት ቁጥር በ2001 ከነበረው በ1.6 እጥፍ በመጨመር 529 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን፣ ይህ ፈጣን እድገት ከግጦሽ መሬት ምርታማነት ጋር ሊመጣጠን አልቻለም።

ይህ አለመመጣጠን በረጅም ጊዜ የምግብ ዋስትና፣ በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ኑሮ እና በሥነ-ምህዳር ዘላቂነት ላይ ከፍተኛ ስጋት የደቀነ ነው።

በሌላ በኩል፣ በደቡባዊ አፍሪካ የሚገኙ ሰፋፊ የግጦሽ መሬቶች ሳይታረሱና በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳይውሉ መቆየታቸው በአህጉሪቱ ያለውን የእንስሳት ሀብት ስርጭትና አጠቃቀም አለመመጣጠን ያሳያል።

በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥ ለግጦሽ መሬቶች መመናመን እንደ “ስጋት ማባባሻ” ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል።

በተለይ በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ የታየው የዝናብ እጥረትና ድርቅ የግጦሽ መሬቶች እንዳያገግሙ በማድረጉ ቀውሱን አባብሶታል። ተመራማሪዎቹ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የእንስሳት ልማት ጫናን ወደ ደቡባዊ አፍሪካ የግጦሽ መሬቶች ማዛወር፣ በየተራ የማጋጥ ዘዴን መከተል እና የእንስሳትን ቁጥር ዝም ብሎ ከመጨመር ይልቅ ጥራትና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው የእንስሳት ውጤቶች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።@SECO

Related

Ethiopia’s Health Spending Set to Surge 73% by 2030, Driven by Government Investment

-Health-related taxes and the exploration of debt-swaps for health...

New ECMA Chief Grants Licences to Two More Investment Banks, Expanding Capital Market Players

The Ethiopian Capital Market Authority (ECMA), under its newly...

Top 10 Largest Cities in Sub-Saharan Africa by 2050: World Bank Population Forecast

The World Bank projects major population growth in Sub-Saharan...

Popular Categories