በአዲስ አበባ ዓለም ባንክ አካባቢ በሚገኘው ደብረ አባይ ቅድስትአርሴማ ገዳም በምንኩስና ይኖራሉ፡፡
እርግጡን እንደማያውቁት ቢናገሩም፣ ዕድሜያቸው ወደ አርባ አምስት ዓመት ገደማ ነው፡፡ ዘጠነኛ ክፍል እንደደረሱ ትምህርት አቆሙ፡፡ ህይወታቸው የምንኩስናው ዓለም ነው፡፡ ነገር ግን ቆይቶ፣ መቼም ለትምህርት አይረፍድምና፣ ከሃያ አምስት ዐመታት በኋላ ወደ ትምህርቱ ተመለሱ፡፡
በገዳሙ ዓቃቢት ነዋይ ናቸውና ስራቸውን በሳይንሳዊው መንገድ ይከውኑ ዘንድ እንዲረዳቸው፣ አስራ ሁለተኛን ክፍል እንደተሻገሩ፣ የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ለመማር ወሰኑ፡፡ የመረጡትም አንጋፋውን ተቋም ኩዊንስ ኮሌጅን ነው፡፡ እነሆ ኮሌጁ ለ26ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው ተማሪዎች አንዷ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ከዚህ በኋላም ስራቸውን በልምድ ሳይሆን በቀሰሙት ጥበብ ለመፈጸም ተዘጋጅተዋል፡፡
ልክ እንደሳቸው ሌሎች መነኮሳትም፣ ቢያንስ የማታ እየተማሩ ዓለማዊውንም ዕውቀት እንዲጨብጡ አበረታታለሁ ብለዋል፡፡

29ኛ ዓመት ምስረታው ላይ የሚገኘው ኩዊንስ ኮሌጅ በቴክኒክናሙያ፣ እንዲሁም በቅድመና ድኅረ ምረቃ ያሠለጥናቸውን 4ሺህ 219 ተማሪዎች ነው ከትላንት በስቲያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ግቢ አዳራሽ ያስመረቀው።
በቴክኒክና ሙያ ትምህርት ዘርፍ 1 ሺህ 740፣ በቅድመ ምረቃ 2 ሺህ 440፣ በድኅረ ምረቃ ደግሞ 45 ተማሪዎችን ነው ጋዋን ያለበሰው። ከምሩቃኑ ወንዶቹ አንድ ሺህም አይሞሉ፤ ሴቶች ይበረክቱበታል።
ኩዊንስ ኮሌጅ በዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር ሞገስ ግርማ መስችነትበ1990 ዓ.ም. አራት ሠራተኞችን ይዞ ነው ማሰልጠን የጀመረው፡፡ አሁን ከአምስት መቶ የበለጡ ቀጥሯል፡፡ ባለፉት 29 ዓመታት ከ54 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስተምሮ ለቁም ነገር አብቅቷል፡፡
በአየር ጤና፣ ፒያሳ አቅራቢያ ዮሐንስ፣ ሜክሲኮ፣ ቃሊቲ፣ ሃናማሪያም፣ ኮልፌና አስኮ አካባቢ ቅርንጫፎች አሉት፡፡ በርቀትም ያስተምራል፡፡ ለአብነት ከቅዳሜዎቹ ተመራቂዎች ውስጥ 763ቱ ባሉበት ሆነው ትምህርቱን የተከታተሉ ናቸው።
በምረቃው ላይ ተገኝተው ለተመራቂዎቹ መልዕክት ያስተላለፉት የሜሪ ጆይ በጎ አድራት ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ ናቸው፡፡
በዚህ አጋጣሚም የኩላሊት ህመም እያስከተለ ስላለው ሃገራዊ ችግር ተመራቂዎቹ እንዲረዱት ለማድረግ ሞክረዋል፡፡
በሃገራችን እንዳሉ ከሚገመቱት 500 ሺህ የኩላሊት ህሙማን፣ በቋሚነት መታጠብ የሚችሉት ሃያ በመቶ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለዚህም ምክንያቱ አገልግሎቱ ከፍተኛ ገንዘብ መጠየቁ ነው፡፡
እሳቸው የሚመሩት ሜሪ ጆይ ሶስት የኩላሊት እጥበት ማዕከላትን ከፍቷል፡፡
ተማሪዎቹ ዛሬ በጤናማነታቸው ዘመን በወር ሁለት መቶ ብር እየከፈሉ የማዕከላቱ አባል ቢሆኑ ወደ ፊት ቢታመሙ እንኳ በነጻ እንደሚታከሙ አብራርተዋል፡፡ ከራሳቸው ባለፈ ማኅበራዊ ትስስራቸውን በመጠቀም ሌሎችንም ለአባልነት እንዲጋብዙላቸው ጠይቀዋል፡፡
የኩላሊት ህመም በአሁኑ ወቅት በወጣቶች ላይ በመበርታቱ ተመራቂዎቹ ጨውና ስኳር የበዛበት፣ እንዲሁም የታሸገ ምግብና መጠጥ እንዳይጠቀሙ መክረዋል፡፡
ለልጆችም እንዳይሰጥ ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡SECO


