የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ላለፉት አራት ወራት ሲጠብቁት የነበረው የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (ኢአይኤች) ውሳኔ ማግኘቱን ኢቲቢዝነስ ቪዉ ከዉስጥ ምንጮቿ ያገኘችው መረጃ ያመለክታል።
የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በባንኩ የደመወዝ እና የጥቅማጥቅም ማሻሻያ ላይ ጥሎት የነበረውን እገዳ አሁን ያነሳ ሲሆን፣ ይህም የባንኩ ሠራተኞች ላስመዘገቡት ታሪካዊ የፋይናንስ አፈጻጸም ያቀረቡት የጥቅማጥቅም ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ አድርጓል።
በባንኩ ማኔጅመንት እና በበላይ አካሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መካከል የነበረው አለመግባባት የተፈጠረው በቀረበው የጭማሪ መጠን እና የሠራተኞች ማበረታቻ ስሌት ቀመር ላይ በነበረ ልዩነት ምክንያት ነው። ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ዘንድ ያለውን የሥራ አፈጻጸም እና የጥቅማጥቅም ሥርዓት ለመገምገም እና ከግል የሥራ አፈጻጸም (KPI) ጋር ይበልጥ ለማስያዝ ባደረገው እንቅስቃሴ ምክንያት ጭማሪው ዘግይቶ ቆይቷል።
ለኢቲቢዝነስ ቪዉ የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ባንኩ ለአዲሱ የ 2019 የበጀት ዓመት ያቀረበው የደመወዝ ማሻሻያ የሦስት እርከን ጭማሪ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ከዚህ ቀደም ይደረጉ ከነበሩት የአንድ ወይም የሁለት እርከን ጭማሪዎች ከፍ ያለ ነው።
በመጀመሪያው ድርድር ላይ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጭማሪው ከሁለት እርከን መብለጥ የለበትም በሚል አቋም ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የባንኩ ማኔጅመንት ባቀረበው የማስረገጫ ነጥቦች ምክንያት በስተመጨረሻ የሦስት እርከኑ ጭማሪ እንዲጸድቅ ሆኗል።
ይህ የተፈቀደው የደመወዝ ጭማሪ እንደየ ሠራተኛው የሥራ መደብ እና ደረጃ ልዩነት የሚኖረው ሲሆን፣ በግምት በአንድ እርከን ከ 7,000 እስከ 10,000 ብር የሚደርስ ሲሆን በወርሃዊ ደሞዝ ላይ እስከ 30 ሺ ብር ብልጫ እንደሚያስገኝ ታውቋል። ጭማሪው የበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ከሆነው ከሐምሌ 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ታስቦ የሚከፈል እንደሚሆን ለመረዳት ተችሏል።
በተጨማሪም ባንኩ ባስመዘገበው ከፍተኛ የትርፍ መጠን ምክንያት ለሠራተኞቹ የሚሰጠው ዓመታዊ ቦነስ ወደ ሦስት ወር ደመወዝ ከፍ እንዲል ተደርጓል። ከዚህ ቀደም ይከፈል የነበረው የሁለት ወር ደመወዝ ቦነስ እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፣ አዲሱ ውሳኔ ከ 52,000 በላይ ለሆኑት የባንኩ ሠራተኞች ትልቅ እፎይታ እና ደስታን ፈጥሯል።
የባንኩ ባልደረቦች እንደገለጹት፣ አብዛኛውን ጊዜ የደመወዝ እርከን ጭማሪ እና ዓመታዊ ቦነስ ከአዲሱ ዓመት መስከረም 1 ቀን በፊት የሚሰጥ ቢሆንም፣ ዘንድሮ በነበረው የክትትል እና የግምገማ ሂደት ምክንያት ለአራት ወራት ዘግይቶ መለቀቁን ተናግረዋል።
የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ይህንን ጭማሪ ያጽድቅ እንጂ፣ ወደፊት የሚደረጉ ማሻሻያዎች በተመሳሳይ ቀመር ይቀጥላሉ ማለት እንዳልሆነ ምንጮች ይጠቁማሉ። በቀጣይ ዓመታት ለሚደረጉ የደመወዝ ጭማሪዎች እና ማበረታቻዎች የሠራተኞች የግል የሥራ አፈጻጸም ምዘና ዋና መስፈርት ሆኖ እንደሚያገለግል ተገልጻል።
ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚያስጠነቅቁት፣ የግል የሥራ አፈጻጸም ምዘናን መተግበር ግልጽ፣ አስተማማኝ እና ከማጭበርበር የጸዳ አሠራርን እንደሚጠይቅ ያሳስባሉ። በተጨማሪም እንደ ንግድ ባንክ ያሉ የፋይናንስ ተቋማት የሥራ ባህሪ ከትራንስፖርት፣ አቪዬሽን ወይም ሎጂስቲክስ ኩባንያዎች ጋር ተመሳሳይ ባለመሆኑ፣ ኢአይኤች በሁሉም ተቋማት ላይ አንድ ዓይነት የግምገማ መስፈርት ከመጠቀም መቆጠብ እንዳለበት ጠቁመዋል።
ይህ የደመወዝ ጭማሪ ውሳኔ የተሰጠው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ 20118 የበጀት ዓመት የ 80.1 ቢሊዮን ብር የጠቅላላ ትርፍ ማስመዝገቡን ይፋ ካደረገ በኋላ ነው። ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 146.3 በመቶ እድገት ያሳየ ነው።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንኩ 272 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ወጪው ደግሞ 192 ቢሊዮን ብር እንደነበር ተገልጻል። ባንኩ 707.4 ቢሊዮን ብር አዲስ ቁጠባ በማሰባሰብ ጠቅላላ የቁጠባ መጠኑን 2.4 ትሪሊዮን ብር ማድረስ ችሏል።
በተጨማሪም 648 ቢሊዮን ብር ብድር የለቀቀ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 91 በመቶ የሚሆነው (588 ቢሊዮን ብር) ለግሉ ዘርፍ የተሰራጨ ነው። የባንኩ የውጭ ምንዛሬ ገቢም ከ5.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማለፉ ተጠቅሷል።SECO


