የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ወይዘሮ ያስሚን ወሀብረቢ እንደገለፁት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሱ ላይ ከ17 ሀገራት የተውጣጡ ከ600 በላይ የሚሆኑ አምራቾች፣ ላኪዎች፣ ዓለም አቀፍ ገዢዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና አምባሳደሮች ይታደማሉ።
በኮንፈረንሱ የፖሊሲና የዓለም አቀፍ ገበያ አዝማሚያ፣ የገበያ መዳረሻዎች፣ የምርት ጥራት መስፈርቶች፣ በዘርፉ እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል።
የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ወደ ትግበራ መግባት ሰፊ እድል እንዳመጣ ተናግረው የአለም ንግድ ድርጅት አባልነትም ወደ መጠናቀቅ ደረጃ የደረሰና ተስፋ ሰጪ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኮንፍረንሱም ለንግዱ ማህበረሰብ ተጨማሪ የገበያ አማራጭ የሚፈጥር በመሆኑ በዘርፉ እየተሳተፉ ያሉ ነጋዴዎች ይህንን እድል እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ የጥራጥሬ እና ቅባት እህል ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኢደኦ አብዲ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ላኪዎች ዓለም አቀፉን የገበያ ፍላጎት ማወቅና መገመት የሚያስችል አቅም መፍጠር፣ የገበያ አዝማሚያን መረዳት፣ ምርትን ማስተዋወቅ እንዲሁም በገዢዎችና ሻጮች መካከል የተጠናከረ የመረጃ ፍሰት እንዲኖር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ኮንፈረንሱ እነዚህን ዕድሎች እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
በምርቶች ላይ እሴት መጨመር ላይ በትኩረት መሰራት እንዲቻል እና ላኪዎቻችን በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ፍሰት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 15ኛውን ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ኮንፈረንስ “የማይበገር ንግድና ዘላቂ የእሴት ሰንሰለቶች” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 15 እስከ 16 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳይንስ ሙዚየም ይካሄዳል።Seco


