በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ አነስተኛ ምርትን በማምረት ወደ ውጪ በመላክ የውጪ ምንዛሬ ማግኛ አድርገውት እንደነበር ተገለጸ
በግብርና ኢንቨስትመንት ስም ከተወሰደው 2 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት የለማው 25 በመቶ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የግብርና ሚኒስቴርንና ተጠሪ ተቋማቱን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድና የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ ላይ ነው የተገለፀው፡፡
የግብርና ሚኒስትር አቶ አዲሱ አረጋ እንደተናገሩት፤ በግብርና ኢንቨስትመንት ስም ከተወሰደው 2 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሄክታር መሬት የለማው 25 በመቶው ነው፡፡
የግብርና አሰራራቸውም ከአርሶ አደሩ ከተሻለ ሁኔታ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በማቅረብ ክፍተት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በትራክተር በማረስ፣ በኮምባይነር በማጨድ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ክፍተቶች እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
ከማክሮ ኢኮኖሚው ሪፎርም በፊት በመሬት ሰርተፍኬትና በይዞታ ገንዘብ ተበድረው የመጥፋት ሁኔታዎች መኖራቸውን በመግለጽ፤ አንዳንዶች አነስተኛ ምርትን በማምረት ወደ ውጪ በመላክ የውጪ ምንዛሬ ማግኛ አድርገውት እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
የግብርናውን ዘርፍ እንደዋና ሥራ ሳይሆን ጊዜዊ ችግር መፍቻ አድርገው የወሰዱ አካላት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በዘርፉ ያለውን ችግር በጥናት በመለየት አስፈላጊው የእርምት ርምጃ እንደሚወሰድ መናገራቸውን የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡


