ኢሰመኮ በጋምቤላ ክልል ያለውን አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ በተመለከተ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በጋምቤላ ከተማ ውይይት ያካሄድኩት በክልሉ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱ ክትትሎችና ምርመራዎች የተደረሰባቸውን ግኝቶች በማቅረብ መልካም እመርታዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እና በአሳሳቢ ጉዳዮች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ለመወትወት ያለመ ነው ብሏል።
ኢሰመኮ በክልሉ ባደረጋቸው ክትትሎችና ምርመራዎች ሁሉም ማረሚያ ቤቶች ምግብ የማያቀርቡ እና በምትኩ የሚሰጠው 75 ብር ካለው የገበያ ዋጋ ጋር ስለማይመጣጠን ታራሚዎችን ለችግር መዳረጉን አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የማደሪያ ክፍሎች የተጨናነቁና ከፍተኛ የንጽሕና ጉድለት ያለባቸው እንዲሁም ለመኝታ አገልግሎት የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች የሌሏቸው መሆኑ፤ የመጸዳጃ ቤቶች የንጽሕና ጉድለት፣ የመጠጥ እና ንጽሕና መጠበቂያ ውሃ አቅርቦት አለመሟላት፣ በቂ የሕክምና አገልግሎት አለመኖር፣ በአንዳንድ ፖሊስ ጣቢያዎችና ማረሚያ ቤቶች አልፎ አልፎ የሚፈጸም ድብደባና ኢ-ሰብአዊ አያያዝ፤ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጋላጭ የሆኑ ተጠርጣሪዎች እና ታራሚዎችን ሁኔታ ያገናዘበ አያያዝ አለማድረግ እንዲሁም የፍትሕ ሂደት መጓተትና ሕገ ወጥ እስራት በክልሉ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው አስታውቋል።
የጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ኢሰመኮ በዝርዝር ያነሳቸው የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በበጎ እንደሚመለከቷቸው ገልጸው በጥንካሬ የቀረቡትን በማስቀጠል እንዲሁም ሊስተካከሉ የሚገቡ የሰብአዊ መብቶች ጉዳዮችን በተሰጡ ምክረ ሐሳቦች መሠረት ክልሉ በዕቅድ በማካተት ፈጣን መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠራ መግለጻቸውን ቅዳሜ ገበያ ከኢሰመኮ ያገኘችው መረጃ ያሳያል።


