አሐዱ ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከግብር በኃላ ከ 399 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታውቋል። ባንኩ በዚሁ 2017 በጀት ዓመት 3.22 ቢሊዮን ብር አዲስ ተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰብ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡን ወደ 7.88 ቢሊዮን ብር ማሳደጉን ያስታወቀ ሲሆን ይህም ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 69.8% ዕድገት እንዳለው አመልክቷል።
አብዛኛው የተቀማጭ ገንዘብ፣ ማለትም 51.5% የሚሆነው፣ ከቁጠባ ሂሳቦች የተገኘ ሲሆን፣ ባንኩ የዲጂታል አገልግሎት መስጫ መንገዶችን በማሻሻል እና የደንበኞችን ቁጥር በማስፋት 390 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን ወደ ቤተሰቡ መቀላቀል ችሏል።
በሌላ በኩል፣ ባንኩ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች 2.6 ቢሊዮን ብር አዲስ ብድር ያቀረበ ሲሆን፣ አጠቃላይ የብድር መጠኑ 4.43 ቢሊዮን ብር ደርሷል።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ከብድሩ ከፍተኛ ድርሻ (57.7%) የተሰጠው ለኤክስፖርት እና ኢምፖርት አገልግሎት ዘርፍ ነው። በዓመቱ ባንኩ 2.16 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ ያገኘ ሲሆን፣ ከግብር በፊት ደግሞ 502.1 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል።


