በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ፈር ቀዳጅ የሆነውን የዳሸን ሱፐር አፕ መተግበሪያ በማስተዋወቅ የዲጂታል ባንክ አገልግሎትን አንድ እርምጃ ያራመደው ዳሸን ባንክ ለ15ኛ ጊዜ የ“ዘ ባንከር” ሽልማትን ማግኘት ችሏል፡፡
ከተለያዩ አገራት የተወጣጡ ባንኮችን በተለያዩ የአፈጻጸም መለኪያዎች በመመዘን ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሚሰጠውና በእንግሊዙ ፋይናንሻል ታይምስ የሚታተመው ዘ ባንከር መጽሔት፣ ዳሸን ባንክ ሁሉን በአንድ የሆነ መተግበሪያ በማስተዋወቁና ለአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ያመጣውን አበርክቶ እንደ ቁልፍ መስፈርት በመውሰድ ለ15ተኛ ጊዜ የ2025 የኢትዮጵያ የዓመቱ ምርጥ ባንክ በሚል ሰይሞታል፡፡
ሽልማቱን በእንግሊዝ ለንደን ከተማ ተገኝተው የተቀበሉት የዳሸን ባንክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው ዓለሙ እንደገለጹት “ዳሸን ባንክ የአመቱ የኢትዮጵያ ምርጥ ባንክ ተብሎ መሸለሙ ባንኩ የኢንዱስትሪውን ቀጣይ ጉዞ በፈጠራ እና በቴክኖሎጂ ለመቅረጽ ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል።” ብለዋል፡፡
ባንኩ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፈር ቀዳጅ በመሆን የሀገሪቱን የመጀመሪያ የባንክ ሱፐር አፕ እና የዙሪያ የቢዝነስ አውቶሜሽን ማሽንን አስተዋውቀናል።” ያሉት አቶ አስፋው፣ “ወደፊትም፣ ሁሉን አካታች፣ ቀልጣፋ እና በዲጂታል መንገድ የተገነባ የፋይናንስ ሥነ-ምህዳር ለመፍጠር እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡


