ፓርቲው እንዳይሰረዝ በ6ኛ ዙር አጠቃላይ ምርጫ በአዲስ አበባ ሊሳተፍ እንደሚችል አስታወውቋል
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በ7ኛ ዙር የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርጫ ላይ መሳተፉን በተመለከተ ኃላፊነት በተሞላበትና መርህ ላይ በተመሰረተ የሚካሄድበትን ስልት መወሰኑን ነው ባወጣው መግለጫ ያስታወቀው፡፡
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረገው ግምገማ በኦሮሚያ፤ በአማራና በሌሎችም ክልሎች በግልጽ በሚታዩ ወታደራዊ ግጭቶች ምክንያት በስፋት በተከሰተ መፈናቀልና በአሰቃቂ የህይወት መጥፋት የተነሳ፤ በመላ አገሪቱ ነጻ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አስቻይ ሁኔታ እንደሌለ ማረጋገጡን ገልጿል፡፡
ፓርቲው የተለያዩ የፖለቲካ መሪዎች በእስር ላይ መቆየታቸው፤ ቢሮዎች መዘጋታቸው፤ እንዲሁም የነጻ ፕሬስና የዜጎች መብቶች ስልታዊ በሆነ መንገድ በመታፈናቸው የብዝሃ-ፓርቲ ዴሞክራሲን ተስፋ ባዶ የሚያደርግ ሁኔታ በመሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩ እጅግ የጠበበ ሆኖ መገኘቱ አረጋግጫለሁ ሲል አስታውቋል፡፡
ፓርቲው በ6ኛ ዙርአጠቃላይ ምርጫ ላይ ባለመሳተፉ እንደ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀዕ 99(1)መ በአዋጅ ቁጥር 1394/2017 ተሻሽሎ-(እንደተሸጋሽገ) “የፖለቲካ ፓርቲዉ በሁለት ተከታታይ የምርጫ ወቅቶች በጠቅላላ ወይም የአካባቢ ምርጫ ዉድድር ሳይሳተፍ የቀረ እንደሆነ ከምዝገባ ይሰረዛል” ስለሚል ብቻ፤ ፓርቲያችን በፌዴራሉ ዋና ከተማ አዲስ አበባ ውስጥና በአንዳንድ ጥቂት አካባቢዎች ሊሳተፍ፤ እስከ ምርጫዉ ጊዜ ድረስ ሁኔታዎች ተስፋ ሰጪና መሠረታዊ በሆነ መንገድ ከተለወጡ ፓርቲው ዉሳኔዉን እንደገና እንደሚያጠን ማዕከላዊ ኮሚቴዉ እንደወሰነ አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ7ኛ ዙር አጠቃላይ ምርጫ ላይ በአዲስ አበባ የምርጫ ክልሎች ላይ እና የደህንነቱ ሁኔታ በምርጫ ለመሳተፍ አስቻይ መሆኑን የሥራ አስፈፃሚዉ ገምግሞ በሚያፀድቃቸዉ የምርጫ ክልሎች ብቻ ዕጩዎቹን እንደሚያቀርብ፣
በሌሎች ሁሉም ክልሎች፣ በተለይም በግጭት በተወጠሩ የኦሮሚያ አካባቢዎችና ከዚያም ውጭ ባሉት የአገሪቱ አከባቢዎች በምርጫው እንደማይሳተፍ፣ ፓርቲው ለነፃና ፍትሓዊ ምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታዎች ማቅረብ እንደሚቀጥል አስታወውቋል፡፡
ፓርቲው በኦሮሚያ እና ጦርነት ዉስጥ ባሉ ሌሎች ክልሎች አፋጣኝና ሊረጋገጥ የሚችል የግጭት ማቆም ስምምነት እንዲደረግ፣ የፖለቲካ እስረኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና ፓርቲዎች ጽ/ቤቶቻቸውን በነጻነት እንዲከፍቱና እንዲያንቀሳቅሱ እንዲፈቀድ፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና የጸጥታ ተቋማት የፖለቲካ ገለልተኝነታቸውን የሚያረጋግጥ እውነተኛና የሚታይ ተቋማዊ ማሻሻያ እንዲያደርጉ፣የቅድመ-ምርጫ ሃደቱን በሙሉ የሚከታተሉና ቅድመ ሁኔታዎቹ መሟላታቸውን የሚያረጋግጡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፤ የአፍሪካ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎችም የረጅም ጊዜ ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎች በአስቸኳይ እንዲጋበዙ ሲል ጠይቋል፡፡©SECO


