የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ፤ የኤርትራ መንግሥት ከድርጅቱ የመውጣት ውሳኔ ያሳለፈው “ተጨባጭ ሃሳቦች ወይም በአይነተኛ ተቋማዊ ወይም የፖሊሲ ማሻሻያዎች ዙሪያ ተሳትፎ” ሳያቀርብ መሆኑን በማንሳት ቅሬታውን ገለጸ።
ኢጋድ ይህንን ውሳኔ በይፋዊ የቃል ማስታወሻ መግባቱን አረጋግጧል። ሆኖም ግን፣ ሴክሬታሪያቱ ለድርጅቱ የተላከው ማስታወሻ ከማንኛውም ቀደም ያለ ውይይት ውጪ መሆኑን ጠቁሟል።
‘ያለፉት ሁለት ዓመታት’ የትብብር እጥረት ኢጋድ እንዳስታወሰው፣ ኤርትራ ለሁለት አሥርት ዓመታት ያህል በራሷ ፍላጎት አባልነቷን ካገደች በኋላ፣ እ.ኤ.አ. ሰኔ 2023 በተካሄደው 14ኛው የልዩ መሪዎች ጉባኤ ላይ በሁሉም አባል አገሮች በሞቃት አቀባበል ወደ ድርጅቱ ተመልሳ ነበር። በዚያን ወቅት፣ መመለሷ “ሁሉን አቀፍነት፣ የክልላዊ ወንድማማችነት እና የታደሰ ትብብር የጋራ ቁርጠኝነት” ማሳያ እንደነበር ድርጅቱ አስታውሷል።
ነገር ግን፣ ኢጋድ ከሰኔ 2023 ጀምሮ ኤርትራ በኢጋድ ስብሰባዎች፣ ፕሮግራሞች ወይም እንቅስቃሴዎች ላይ አለመሳተፏን በጸጸት ገልጿል። ሴክሬታሪያቱ በዚህ ጊዜ ሁሉ “ትዕግሥትና በጎ ፈቃድ” ሲያሳይ እንደቆየ እና ለገንቢ ተሳትፎ ክፍት እንደነበር አሳውቋል።
ይህ የተባለዉ የኤርትራ በይፋ ከኢጋድ አባልነት መዉጣቷን ማሳወቋን ተከትሎ ነዉ ። የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣዉ መግለጫ ፤ ውሳኔው የመጣው ኢጋድ በኤርትራ በኩል የቀረቡትን የለውጥ ጥሪዎች ችላ በማለቱ እና “በሕግ የተሰጠውን ግዴታዎች በመጣሱ” እንደሆነ አመልክቷል።
ኤርትራ በተለይም እኤአ ከ2005 ዓ.ም. ወዲህ ኢጋድ የክልሉን ሕዝቦች ምኞት ማሟላት ሳይችል ቀርቷል ከሚል እምነት ላይ ተነስታለች፤ በምትኩም “ዒላማ በተደረጉ አባል አገሮች ላይ በተለይም ኤርትራ ላይ የሚሠራ መሣሪያ በመሆን ጎጂ ሚና ተጫውቷል” በማለት ወቅሳለች።
ኤርትራ ድርጅቱ “ምንም የሚታይ ስትራቴጂካዊ ጥቅም” እንደማይሰጥ እና “ሕጋዊ ሥልጣኑን እና ኃላፊነቱን ያጣ” ነው ስትል አባልነቷን ሰርዛለች።
ምንም እንኳን ውጥረቱ ቢኖርም፣ የኢጋድ ሴክሬታሪያት ውሳኔውን የወሰደው “ምንም ዓይነት ውይይት ወይም የለውጥ ሀሳብ ሳያቀርብ ነው” በማለት ቢወቅስም፣ “ግንኙነቱን እንደሚቀጥል” አስታውቋል።
ኢጋድ የኤርትራ መንግሥት “ዉሳኔዉን እንደገና እንዲመለከት እና ለሰላም፣ መረጋጋት እና የክልሉን ልማት የሚረዱ የጋራ ግቦችን ለማራመድ ሙሉ በሙሉ በበጎ ፈቃድ ወደ ድርጅቱ እንዲመለስ” ጥሪ አቅርቧል።Seco


