የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የጂቡቲ መንግሥት እና የኤሚሬትስ ናሽናል ኦይል ካምፓኒ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አዲስ አበባ ላይ ባደረጉት ስብሰባ፣ ነዳጅን በባቡር መስመር የማጓጓዝ አገልግሎት ዳግም ለማስጀመር በሚያስፈልጉ ቁልፍ የፋይናንስ ዝግጅቶች እና የወጪ አወቃቀሮች ላይ መምከራቸው ተገልጿል።
የዚህ ስልታዊ ፕሮጀክት መነቃቃት በሀገር ውስጥ የነዳጅ ማጓጓዣ ወጪን በመቀነስ የገበያ ዋጋን የማረጋጋት ከፍተኛ ተስፋ እንዳለው ተጠቁሟል።
በጂቡቲ የኢነርጂ ሚኒስትር ዮኒስ አሊ ጌዲ እና የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በጋራ በተመራው በዚህ ስብሰባ፣ የተጣራ የነዳጅ ውጤቶችን ከጂቡቲው ዶራሌህ ተርሚናል እስከ ኢትዮጵያ አዋሽ በሚገኙ የነዳጅ ማከማቻዎች በባቡር መስመር የማጓጓዝ ስራን ዳግም ማስጀመር ላይ ትኩረት ተደርጓል።
በአሁኑ ጊዜ ነዳጅ በታንከር መኪናዎች በብዙ ውጣ ውረድ በመንገድ ላይ የሚጓጓዝ በመሆኑ፣ የባቡር አገልግሎት መጀመር የነዳጅ ማጓጓዣን ይበልጥ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ እና ወጪ ቆጣቢ ያደርገዋል። ይህ ቅልጥፍና በነዳጅ ዋጋ ላይ ያለውን ጫና በእጅጉ ይቀንሰዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ስምምነቶችን ዳግም ማስጀመርን በሚመለከት ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ የውይይቱ ዋና አጀንዳዎች ደግሞ የፋይናንስ ዝግጅቶች፣ የወጪ አወቃቀሮች እና የዋጋ አወሳሰን ጉዳዮች ነበሩ።
የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ የነዳጅ ትራንስፖርትን ማረጋገጥ እና አቅሙን ማስፋት የኢትዮጵያን የገበያ ፍላጎት ለማሟላት መሠረታዊ መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ፣ የጂቡቲ ኢነርጂ ሚኒስትር ዮኒስ አሊ ጉኤዲ ፕሮጀክቱ ሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚ በይበልጥ የሚያዋህድ በመሆኑ ያለ መዘግየት እንዲተገበር አሳስበዋል። “እያንዳንዱ መዘግየት የፕሮጀክቱን ወጪ ይጨምራል። ለሁለቱ አገሮች ጥቅም ሲባል በፍጥነት እርምጃ መውሰድ አለብን” በማለት የመፍትሔ ፍጥነት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና የENOC ባለሥልጣናት ከሁለቱ መንግሥታት ተወካዮች ጋር በመሆን፣ ስምምነቶቹን የመጨረሻ ቅርፅ ለማስያዝ እና የዚህን ስልታዊ ፕሮጀክት አፈጻጸም ለማፋጠን የሚያስችል ተግባር ልዩ ግብረ ኃይል ለመመስረት ተስማምተዋል።
ይህ ፕሮጀክት፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ምርት ወደ ውጭ የሚላከውና ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው በጂቡቲ ወደቦች በኩል በሚያልፈው በአዲስ አበባ–ጂቡቲ የባቡር መስመር በኩል ስለሆነ፣ የክልላዊ ንግድን እና የኃይል ትስስርን ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት የዳዉን አፍሪካ ዘገባ ያሳያል።
የተካሄደው ስብሰባ በጉዳዩ ውስጥ ያሉትን ቁልፍ ተዋናዮች በሙሉ አሰባስቧል፣ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ፣ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ፣ የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር እንዲሁም በዶራሌህ በሚገኘው ኤች.ዲ.ቲ.ኤል. ተርሚናል ውስጥ ዋነኛ ድርሻ ያለው የኢሚሬትስ ቡድን ኢኖክ ተገኝተዋል።
የባቡር መስመሩ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ያለውን ፈተና በመቅረፍ ለሁለቱ አገሮች የጋራ ጥቅም ያረጋግጣል ተብሎ ይጠበቃል።@Seco


