ከ145 በላይ አገራት የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች በውጭ አገራት ተጨማሪ የኮርፖሬት ግብር እንዳይከፍሉ በሚያስችል የጥቅም ማረጋገጫ (Exemption) ላይ መስማማታቸው ተገለጸ። ይህ ስምምነት እ.ኤ.አ. በ2021 ተደርሶ የነበረውን ታሪካዊ የዓለም አቀፍ ግብር ስምምነት የሚያለሰልስ መሆኑ ተጠቁሟል።
የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ድርጅት እንዳስታወቀው፤ ዋና መሥሪያ ቤታቸው “አነስተኛ የግብር መስፈርትን በሚያሟሉ” አገራት ውስጥ ለሚገኙ ኩባንያዎች “ደህንነቱ የተጠበቀ መጠለያ” እንዲኖር ተስማምቷል።
ይህም የአሜሪካ ኩባንያዎች በሌሎች አገራት ውስጥ ከሚጣለው 15 በመቶ ዝቅተኛ የዓለም አቀፍ የኮርፖሬት ግብር ነፃ እንዲሆኑ ዕድል ይሰጣል።
ይህ ለውጥ የመጣው በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ግፊት መሆኑ ተገልጿል። የአሜሪካ መንግሥት ስምምነቱን በመቃወም በኩባንያዎቼ ላይ አድልዎ ይፈጸማል በሚል “የበቀል ግብር” ለመጣል ሲዝት መቆየቱ ይታወሳል።
ቻይና፣ ፖላንድ፣ ኢስቶኒያ እና ቼክ ሪፐብሊክ መጀመሪያ ላይ ስምምነቱን ተቃውመው የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ተቃውሟቸውን አንስተዋል።
ቻይና እንደ አሜሪካ ሁሉ ለኩባንያዎቿ ተመሳሳይ ጥቅማጥቅም እንዲሰጣት ስትጠይቅ የነበረ ሲሆን፣ የአውሮፓ አገራት ደግሞ የስምምነቱ መላላት በንግድ ተወዳዳሪነታቸው ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ተፅዕኖ ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።
የግብር ፍትህ ተሟጋቾች በበኩላቸው፤ “አሜሪካ የፈለገችውን አግኝታለች፣ ሌሎች አገራትም ተስማምተዋል” ሲሉ ስምምነቱን ነቅፈዋል። ይሁን እንጂ የኦኢሲዲ የግብር ኃላፊ ማናል ኮርዊን “ስምምነቱ ፖሊሲውን ለማጠናከር እንጂ ዓለም አቀፍ ዝቅተኛ ግብርን ለመተው አይደለም” ሲሉ ተከራክረዋል።@SECO


