ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ በጋራ የሚገነቡትና 5 ቢሊዮን ዶላር የወጣበት የምስራቅ አፍሪካ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ በተያዘው በፈንጆቹ በጀት ዓመት የመጀመሪያውን ድፍድፍ ነዳጅ ለዓለም ገበያ ማቅረብ እንደሚጀምር ተገለጠ።
በዓለም ላይ ረጅሙ የሚሞቅ የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ተብሎ የተጠቀሰው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት፣ ምስራቅ አፍሪካን በዓለም አቀፍ የነዳጅ ንግድ ካርታ ላይ ጉልህ ስፍራ የሚያሰጣት ከመሆኑም በላይ በቀጣናው ያለውን የኢነርጂ ትስስር ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግራል ተብሎ ታምኖበታል።
ከኡጋንዳው አልበርቲን ግራበን ተነስቶ 1,443 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ታንዛኒያ ወደሚገኘው የህንድ ውቅያኖስ ታንጋ ወደብ የሚደርሰው ይህ ቧንቧ፣ እስከ ታኅሣሥ 2025 መጨረሻ ድረስ 80 በመቶ ያህሉ ግንባታው መጠናቀቁን የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።
የኡጋንዳ የነዳጅ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኤርነስት ሩቦንዶ እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ቁልፍ ሞተር ሲሆን፣ እስካሁንም 3.3 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ፈሶበታል።
የሁለቱ ሀገራት የኢነርጂ ሚኒስትሮች በዳሬሰላም ባደረጉት ስብሰባ፣ ግንባታው በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት ላይ እንደሚገኝና በመጪው ሐምሌ ወር ለሥራ ሙሉ በሙሉ ዝግጁ እንደሚሆን ገልጸዋል።
ይህ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር በቀን እስከ 230,000 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማስተላለፍ አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ ለኡጋንዳ በሀገሪቱ የሚገኘውን 6.5 ቢሊዮን በርሜል የነዳጅ ክምችት ወደ ገንዘብ ለመቀየርና አዲስ ነዳጅ አምራች ሀገር ሆና እንድትወጣ ያስችላታል።
ለታንዛኒያም ቢሆን ፕሮጀክቱ እስካሁን በግብርና እና በተለያዩ ክፍያዎች 19.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኘ ሲሆን፣ ለዜጎቿም ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ቧንቧው የኡጋንዳ ነዳጅ ወፍራም በመሆኑ፣ ነዳጁ ሳይረጋ እንዲፈስ በ50 ዲግሪ ሴልሺየስ ሙቀት ውስጥ እንዲያልፍ ተደርጎ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገነባ መሆኑም ተመልክቷል።@SECO


