የቻይና፣ የሩሲያ እና የኢራን የባሕር ኃይል የጦር መርከቦች “የሰላም ፈቃድ 2026” መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ልምምድ ላይ ለመሳተፍ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ሲሞን ታውን የባሕር ኃይል ጣቢያ ደርሰዋል።
ለአንድ ሳምንት የሚቆየውና ዛሬ በይፋ የሚጀመረው ይህ ልምምድ፣ በዋናነት የንግድ መርከቦች የሚያልፉባቸውን መስመሮች ደኅንነት ለመጠበቅና በባሕር ላይ የሚፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችን የመከላከል ዓላማ እንዳለው የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በልምምዱ ላይ ከሦስቱ አገራት በተጨማሪ ሌሎች የብሪክስ አባል አገራት ተወካዮችና ታዛቢዎች እንደሚሳተፉም ተገልጿል።
ይህ ወታደራዊ ልምምድ እየተካሄደ ያለው አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ ወታደራዊ ጥቃት በመሰንዘር ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ተከትሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጥረት በነገሠበት ወቅት ነው።
የትራምፕ አስተዳደር በቬንዙዌላ ላይ የሚወስደውን እርምጃ በማጠናከር በዓለም አቀፍ ውቅያኖሶች ላይ የነዳጅ ጫኝ መርከቦችን እየያዘ ሲሆን፣ በቅርቡም የሩሲያ ሰንደቅ ዓላማ ያረፈባትን መርከብ መቆጣጠሩ ይታወሳል።
የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ልምምዱ ቀድሞ የታቀደ እንጂ አሁን ካለው ውጥረት ጋር ግንኙነት የለውም ቢልም፣ እርምጃው አሜሪካ በደቡብ አፍሪካ ላይ ያላትን ቅሬታ ይበልጥ ሊያባብሰው እንደሚችል ተሰግቷል።
በደቡብ አፍሪካ ውስጥም ቢሆን ሩሲያና ኢራንን ያካተተ ወታደራዊ ልምምድ ማስተናገዱ ከፍተኛ የፖለቲካ ክርክር አስነስቷል። ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግሥት “ገለልተኛ ነኝ” የሚለውን መርህ በመጣስ ማዕቀብ ከተጣለባቸው አገራት ጋር ወታደራዊ ግንኙነቱን እያጠናከረ ነው በሚል እየተቹት ይገኛሉ።
በአንጻሩ በፕሪቶሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ደጃፍ ላይ የተሰበሰቡ ሰልፈኞች፣ አሜሪካ በቬንዙዌላ ላይ የፈጸመችውን ጣልቃ ገብነትና የፕሬዝዳንት ማዱሮን መታፈን በማውገዝ ለቬንዙዌላ ያላቸውን አብሮነት እየገለጹ ነው።@SECO


