ኢትዮ ቴሌኮም በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የኤም-ፔሳ አገልግሎት ላይ የወሰደው እርምጃ የደንበኞችን ደህንነትና የኩባንያውን መሰረተ ልማት ከመጠበቅ አኳያ የተከናወነ እንጂ ሆን ተብሎ ኔትወርክን የመዝጋት ፍላጎት እንዳልነበረው አስታወቀ።
ይህ የተገለጸው፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኩባንያ፣ “ኤምፔሳ ለሁሉም” ብሎ የሰየመው አዲሱ የገንዘብ መገበያያና ማስተላለፊያ መተግበሪያ የኢትዮ ቴሌኮም ቁጥር ላላቸው ተገልጋዮች አገልግሎት እንደይሠጥ እንደታገደበት ከሳወቀ ከወራት በኃላ ነዉ።
ይህ መተግበሪያ፣ የሳፋሪኮም እና የኢትዮ ቴሌኮም ስልክ ቁጥር ለያዙ ሁሉም የስልክ ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት እንዲችል ሆኖ የተሠራ እንደሆነ ተቋሙ መግለፁ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ የኢትዮቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ የተቋማቸዉን የበጀት ዓመቱን 6 ወራት አፈፃፀም በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት ወቅት እንደገለፁት “ኩባንያው በሃላፊነት የሚያስተዳድራቸውን ደንበኞች ከስርዓት ውጭ አገልግሎት ለመስጠት መሞከር ከኮምፕሊያንስና ከሙያ ስነ-ምግባር ውጭ ነው” ብለዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ኢትዮ ቴሌኮም በዲስፕሊንና በፕሮፌሽናሊዝም ለሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ፣ ለብሔራዊ ባንክ እና ለኢንሳ በጽሁፍ ማሳወቁን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ዙር በቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ ድርጊቱ ቆሞ የነበረ ቢሆንም፣ ለሁለተኛ ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ በመከሰቱ ተቋሙ ደንበኞቹንና የገነባውን መሰረተ ልማት ለመጠበቅ ሲል እርምጃ መውሰዱን አስታውቀዋል።
“ብዙዎች ኢትዮ ቴሌኮም ኔትወርክ ዘጋብኝ በሚል ነው የተረዱት፤ ነገር ግን ኔትወርክ አልተዘጋም” ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ሳፋሪኮም የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞችን ያለ ስምምነት በመንጠቅ አገልግሎት ለመስጠት መሞከሩ በሌሎች ሃገራትም የማይሰራና ተገቢ ያልሆነ አሰራር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማቱን ለማጋራት ዝግጁ ቢሆንም፣ ማንኛውም ተፎካካሪ ድርጅት የኢንዱስትሪውን ስርዓትና የደንበኞችን ደህንነት ማክበር እንዳለበት በማሳሰቢያቸው ጠቁመዋል።@SECO


