የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤስኪያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ከአሜሪካ ጋር ፍትሐዊ ድርድር እንዲደረግ ማዘዛቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ አስታወቁ።
ፕሬዝዳንቱ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሉት “ወዳጅ መንግሥታት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ በመስጠት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ ጥቅማችንን በሚያስከብር ሁኔታ ለፍትሐዊ እና ለትክክለኛ ድርድር ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታን እንዲያመቻቹ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ” ብለዋል።
የኢራኑ ፕሬዝዳንት ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ መሆናቸውን ያስታወቁት፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተወካያቸው ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን እና ግንኙነቱ ጥሩ ውጤት እንደሚያስገኝ ተስፋቸውን ከገለጹ በኋላ ነው።
እንደ ቢቢሲ ዘገባ፤ ትራምፕ አሁንም የሚደረጉ ንግግሮች ውጤት የማያስገኙ ከሆነ “መጥፎ ነገር ይከሰታል” በማለት በድጋሚ አስጠንቅቀዋል።
በቀጣይ ቀናት ምናልባትም በመጪው አርብ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ ቱርክ ኢስታምቡል ውስጥ ሊገናኙ ቀጠሮ እንደተያዘላቸው ዘገባዎች እየወጡ ነው።@SECO


