በኢራን እና በእስራኤል መካከል ያለው ጦርነት ዓለም አቀፍ የንግድ ፍሰትን እያናጋ ባለበት በዚህ ወቅት፣ በርካታ የአፍሪካ መንግስታት የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን ለመከላከል ወደ ዳንጎቴ የነዳጅ ማጣሪያ እና ፔትሮኬሚካል ተቋም ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑ ተገለጸ።
በተለይም የደቡብ አፍሪካ መንግስት ከናይጄሪያው ግዙፍ ማጣሪያ ጋር የ12 ወራት የነዳጅ አቅርቦት ስምምነት ለመፈረም ድርድር እያደረገ መሆኑ ታውቋል።
የኢነርጂ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ በተለይ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት 75% የሚሆነውን የተጣራ ነዳጅ ከመካከለኛው ምስራቅ የሚያስገቡ በመሆናቸው ለዚህ ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ ሆነዋል።
ይህንን ተጋላጭነት ለመቀነስም ጋና እና ኬንያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወደ ዳንጎቴ ማጣሪያ አቅንተዋል።
ቢሊየነሩ አሊኮ ዳንጎቴ በሰጡት ቃለ ምልልስ “በአሁኑ ወቅት ትልቁ ፈተና የነዳጅ ዋጋ ሳይሆን አቅርቦት ማግኘት ነው” በማለት ሁኔታው ለተወሰነ ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል፣ የቀውሱ ተጽዕኖ በኢትዮጵያም መታየት የጀመረ ሲሆን፣ ባለስልጣናት የነዳጅ ማደያዎች ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ቅድሚያ እንዲሰጡና ዜጎችም ነዳጅን በቁጠባ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።
በሶማሊያ ደግሞ የነዳጅ ዋጋ በእጥፍ መጨመሩ ተነግሯል። በቀን 650,000 በርሜል የማጣራት አቅም ያለው የዳንጎቴ ተቋም፣ ከናይጄሪያ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ውጭ ያለውን ምርት ለጎረቤት ሀገራት ለማቅረብ እየተዘጋጀ ሲሆን፣ ይህም አፍሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ያላትን ጥገኝነት ለመቀነስ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ይታመናል።

በሌላ በኩል በናይጄሪያ የሚገኘው ግዙፉ የዳንጎቴ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ተከትሎ፣ በ12 ዙር ጭነቶች በአጠቃላይ 456,000 ቶን የተጣራ ነዳጅ ለአምስት የአፍሪካ ሀገራት ማለትም ለኮትዲቩዋር፣ ካሜሩን፣ ታንዛኒያ፣ ጋና እና ቶጎ በማቅረብ የኤክስፖርት ገበያውን በከፍተኛ ሁኔታ ማስፋፋቱ ተሰምቷል።
በቀን 650,000 በርሜል የማጣራት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ግጭት ምክንያት በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል የሚደረገው የነዳጅ ዝውውር መስተጓጎሉን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከፍተኛ ጥራት ያለው (Euro V standard) ቤንዚን ለአህጉሪቱ ሀገራት ማቅረብ መቻሉ ተገልጿል።
ይህም ከአውሮፓና ከመካከለኛው ምስራቅ የሚመጣውን ረጅም የትራንስፖርት ጉዞና ወጪ በመቀነስ ለአፍሪካ የነዳጅ ዋስትና ትልቅ ተስፋ መሆኑ ተመላክቷል።@SECO


