በኢቢቪ ዘጋቢ
የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ (EIB) የልማት ክንፍ የሆነው ኢአይቢ ግሎባል (EIB Global) በኢትዮጵያ ውስጥ በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩና ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለሚልኩ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚውል የ40 ሚሊዮን ዩሮ የፋይናንስ ድጋፍ ስምምነት ከዘመን ባንክ ጋር ተፈራረመ።
በአዲስ አበባ በተካሄደው የአውሮፓ ህብረት-ኢትዮጵያ የንግድ ፎረም ላይ ይፋ እንደተደረገው፣ ኢአይቢ ግሎባል የ20 ሚሊዮን ዩሮ የብድር መስመር ለዘመን ባንክ ያቀረበ ሲሆን ባንኩም በተመሳሳይ የራሱን 20 ሚሊዮን ዩሮ በማከል ለዘርፉ ያውላል።
ይህ ስምምነት ኢአይቢ ግሎባል በኢትዮጵያ ለሚገኝ የግል የንግድ ባንክ በቀጥታ የሰጠው የመጀመሪያው ብድር በመሆኑ በኢኮኖሚ ትብብሩ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሆኗል።
ይህ የብድር ድጋፍ በዋናነት ለቡና እና ለጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ላኪዎች የሚውል ሲሆን፣ ቢያንስ 30 በመቶ የሚሆነው ፋይናንስ በሴቶች ለሚመሩ ወይም ለሴቶች የሥራ ዕድል ለሚፈጥሩ ድርጅቶች እንዲውል ተለይቷል።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የሚያስችሉና የአካባቢ ጥበቃን ከግምት ውስጥ ያስገቡ የግብርና ሥራዎች የ30 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ እና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነር ጆሴፍ ሲኬላ እንደገለጹት፣ ይህ ኢንቨስትመንት የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከመጨመር ባለፈ በግብርናው ዘርፍ ለሚሰማሩ ወጣቶችና ሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥርና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያፋጥን ነው።@SECO


