ኢትዮ ቴሌኮም ባለአክሲዎኖችን በይፋ ተቀበለ

ትርፍ የመከፈል መብት ከዘንድሮው በጀት አመት ጀምሮ የሚታሰብ ይሆናል

ኢትዮ ቴሌኮም በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የተመዘገበ የመጀመሪያው የመንግስት ኩባንያ ነው

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ

ግዙፉ እና ከፍተኛ ትርፍ በማስገባት ቀዳሚ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮም ከአመት በፊት በተጠናቀቀው የመጀመሪያ የአክሲዎን ሽያጭ ድርሻ የገዙ ባለሃብቶች የትርፍ ክፍፍል ተጠቃሚ መሆን እንደሚጀምሩ አስታወቀ፡፡

የቴሌኮም ኩባንያው ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት አምና በተጠናቀቀው እና ለመጀመሪያ ጊዜ ባከናወነው የአክሲዎን ሽያጭ በድምሩ 10.7 ሚሊዮን አክሲዮኖችን ድርሻ ለገዙ በመላ ሀገሪቱ ለሚገኙ 47,377 ዜጎች በይፋ የድርጅቱ ባለቤት መሆን መቻላቸውን አስታውቋል፡፡

የ132 አመታት እድሜ ጠግብ ኩባንያ አመራር ይፋ እንዳደረገው ኩባንያው ባለፉት ወራት ባለአክሲዮኖች የተቋሙ ባለቤት የሚሆኑበትን ማረጋገጫ ለመስጠት የሚያስችሉ መጠነ-ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ በተለይም የባለአክሲዮኖችን መረጃዎች (KYC) በመመርመር እንዲሁም ከባለአክሲዮኖች ጋር በመነጋገር ያልተሟሉ መረጃዎችን የማሟላት ተግባራትን አከናውኗል።

በተጨማሪም ባለአክሲዮኖች በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ መደላድሎችን ለመፍጠር፣ የተሸጡ አክሲዮኖች ድልድል በካፒታል ገበያ ባለሥልጣን እንዲጸድቅና የተደለደሉ አክሲዮኖች በማዕከላዊ የሰነዶች ሙዓለ ነዋዮች ግምጃ ቤት (Central Securities Depository) እንዲመዘገቡ ተደርጓል።

በዚህም መሠረት አጠቃላይ አክሲዮን ከገዙ 47,377 ዜጎች ውስጥ 45,366 (95.8 በመቶ) የሚሆኑት የባለቤትነት ማረጋገጫና አክሲዮኖችን ወደ ዲጂታል የመቀየር (Dematerialization) ሂደታቸውን ሙሉ በሙሉ አጠናቀዋል። እነዚህ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሂደታቸውን ያጠናቀቁ ዜጎች በገንዘብ ሲሰላ 3.04 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 10.1 ሚሊዮን አክሲዮኖች ባለቤት መሆናቸው ተረጋግጧል።

በመሆኑም በዛሬው ዕለት፣ የኢትዮ ቴሌኮም ባለአክሲዮኖች በኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ነዋዮች ገበያ (ESX) ላይ አክሲዮናቸውን ማንቀሳቀስ የሚያስችላቸው ዝግጅት መጠናቀቁንና በይፋ ለግብይት ዝግጁ መሆናቸውን ነው የገለጸው፡፡

ባለአክሲዮኖች አክሲዮኖቻቸውን ተፈጻሚነት ባላቸው ህጎች መሠረት የመሸጥ፣ የመግዛት እንዲሁም የማስተላለፍ (Transfer) መብት የሚያገኙ ይሆናል። አክሲዮኖቻቸውን በሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ላይ ለመሸጥም ሆነ ተጨማሪ ለመግዛት፤ በመጀመሪያ በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ፈቃድ ከተሰጣቸው አገበያዮች ወይም የኢንቨስትመንት ባንኮች (Licensed investment bank, Brokers/Dealers) ዘንድ በመቅረብ የንግድ አካውንት መክፈት እንዳለባቸው ተገጧል፡፡

የባለቤትነት ድርሻቸውን ወደ ዲጂታል የመቀየር (Dematerialization) ሂደት ያጠናቀቁ ባለአክሲዮኖች፤ የባለቤትነት መብታቸው ከያዝነው በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ የሚከበርና የሚጠበቅላቸው ሲሆን፡፡ የትርፍ ክፍፍልም ያገኛሉ፡፡

በሌላ በኩል፣ በብሔራዊ መታወቂያ መረጃ አለመሟላት ምክንያት ገና ያልተረጋገጡ 1,646 ባለአክሲዮኖች መረጃዎቻቸውን በአፋጣኝ እንዲያሟሉ ኩባንያው ጥሪ አቅርቧል፡፡

እንዲሁም የኢትዮ ቴሌኮም አክስዮኖችን ለመግዛት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን የማያሟሉ 248  (105 ሺህ አክሲዮኖች) የአክስዮን ግዢ ጥያቄ አቅራቢ የውጪ ዜጎች የከፈሉት ገንዘብ ተረጋግጦ ተመላሽ ይደረጋል ነው የተባለው።

የዛሬው ይፋዊ መግለጫ ባለአክሲዮኖች በሁለተኛ ገበያ ላይ አክሲዮኖችን በመግዛት፣ በመሸጥ ወይም ማስተላለፍ መቻል ዜጎች በዲጂታል ኢኮኖሚው ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በር የሚከፍት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው፣›› በማለት የኩባንያው ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እለቱን ገልፀውታል፡፡

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ኢትዮ ቴሌኮም አ.ማ በዋናው የገበያ መድረክ ላይ በይፋ መመዝገቡን አስታወቀ::

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ጥላሁን እስማኤል እንዳሉት “የኢትዮ ቴሌኮም በግብይቱ ዋና ገበያ ላይ መመዝገብ ለገበያው ትልቅ ድል እቻ ሳይሆን፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደ ገበያው በመምጣት የኢትዮጵያ መንግስት የካፒታ ገበያን ለማሳደግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እና አርአያነት ያለው የመጀመሪያ እርምጃ ነው፣” ብለዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የተመዘገበ የመጀመሪያው የመንግስት ኩባንያ ነው፡፡©SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 220 ቦታዎች የሊዝ ጨረታ አወጣ

​የአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በዘጠኝ ክፍለ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

Popular Categories