በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በፓጋክ አካባቢ ለዓመታት ሲንቀሳቀስ የነበረው የግብፅ ወታደራዊ እና የደህንነት ካምፕ እንዲዘጋ የጁባ መንግስት መወሰኑ ተሰማ። ይህ ውሳኔ በምስራቅ አፍሪካ እና በዓባይ ወንዝ ዲፕሎማሲ ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሆን፣ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትስስር ይበልጥ እንድታጠነክር በር የከፈተ ስልታዊ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።
ካምፑ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ 260 የሚጠጉ የግብፅ ወታደራዊ አሰልጣኞች፣ ቴክኒሻኖች እና የደህንነት መኮንኖችን ይዞ የቆየ ሲሆን፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሚገኝበት ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቅርብ በመሆኑ ግብፅ በግድቡ እና በናይል ወንዝ ፍሰት ላይ የስለላ ስራዎችን ለመስራት ስትጠቀምበት እንደነበር ይነገራል።
የካምፑ መዘጋት በካይሮ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠረ ሲሆን፣ የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲ ከከፍተኛ የደህንነት እና የወታደራዊ መሪዎቻቸው ጋር አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።
የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ለደቡብ ሱዳን ውሳኔ ዋነኛው ምክንያት በአገሪቱ ላይ የተደቀነው ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ነው። ደቡብ ሱዳን ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን ብሄራዊ ገቢዋን የምታገኘው በሱዳን በኩል ወደ ፖርት ሱዳን በሚላክ ድፍድፍ ዘይት ሽያጭ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በሱዳን ባለው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮቿ በመውደማቸው ገቢዋ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
ይህን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም ጁባ አማራጭ የንግድ እና የነዳጅ ማጓጓዣ መስመሮችን ለመፈለግ የተገደደች ሲሆን፣ የጋምቤላ-ፓጋክ ኮሪደር ለወደፊቱ የነዳጅ ኤክስፖርት እና ቀጣናዊ የንግድ ትስስር ቁልፍ ተስፋ ሆኗል።
በመሆኑም ደቡብ ሱዳን የራሷን የኢኮኖሚ ህልውና ለማስጠበቅ የግብፅን የፖለቲካ ፍላጎት ወደ ጎን በመተው ከኢትዮጵያ ጋር በሃይል እና በመሰረተ ልማት ዘርፎች ለመተባበር ቆርጣ ተነስታለች።
በተጨማሪም ይህ እርምጃ በናይል ተፋሰስ አገራት መካከል ያለውን የዲፕሎማሲ ፉክክር አቅጣጫ የሚቀይር ነው። ደቡብ ሱዳን በቅርቡ የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን በመፈረም የኢትዮጵያን ጎራ መቀላቀሏ ይታወሳል። ይህ ስምምነት ግብፅ እና ሱዳን በናይል ወንዝ ላይ የነበራቸውን ብቸኛ ባለቤትነት ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርግ ሲሆን፣ ጁባ የዚህ ስምምነት አካል መሆኗ እና የግብፅን የደህንነት ካምፕ መዝጋቷ ለኢትዮጵያ ታላቅ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ተወስዷል።@seco


