የኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እስከ ፈረንጆቹ 2035 ድረስ መላውን የሀገሪቱን ክፍል አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ እየቀረጸ መሆኑን አስታወቀ። ለዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግ የተገለጸ ሲሆን፣ ዘርፉን ለግል ባለሀብቶች ክፍት የማድረግ እቅድም ተካቷል።
ይህ ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ያለው የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ መሰረተ ልማቶችን የሚመራው “የብሔራዊ የኤሌክትሪክ ፕሮግራም” (NEP) በሦስተኛው ምዕራፍ ስር ነው።
አዲሱ ምዕራፍ በቀደሙት ሁለት ምዕራፎች የተለዩትን የፋይናንስ እና የአፈጻጸም ክፍተቶችን ለመሙላት ታሳቢ ተደርጎ የተነደፈ መሆኑ ተገልጿል።
በፕሮግራሙ አፈጻጸም ዙሪያ በተካሄደ ሀገር አቀፍ ወርክሾፕ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢነርጂ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ፣ አስተማማኝ እና ተመጣጣኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሦስተኛው ምዕራፍ ንጹህ ኃይልን ማስፋፋት፣ የአየር ንብረት ተጽዕኖዎችን መቋቋም፣ የኃይል አጠቃቀምን ውጤታማ ማድረግ እና የዘርፉን ዲጂታላይዜሽን ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
መንግስት የኃይል ማመንጫዎችን እና ተያያዥ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማበረታታት የኢትዮጵያን የኢነርጂ ፖሊሲ በመገምገም ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ፣ በአዲሱ ፕሮግራም አዳዲስ የኃይል ማመንጫዎች፣ የማስተላለፊያ መስመሮች እና የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።@seco


