የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ የውጭ ሀገር ዜጎች በችርቻሮ ንግድ እና በጎዳና ላይ ንግድ ላይ እንዳይሰማሩ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላለፉ። ፕሬዚዳንቱ በናይሮቢ ከትናንሽ ንግድ ባለቤቶች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ከመጪዉ ከሰኞ ጀምሮ የውጭ ዜጎች በዝቅተኛ ካፒታል የሚሠሩ ትናንሽ ንግዶችን በሙሉ እንዲዘጉ አሳስበዋል።
መንግሥት የውጭ ኢንቨስትመንትን በደስታ እንደሚቀበል የገለጹት ፕሬዚዳንት ሩቶ፣ ነገር ግን የውጭ ዜጎች ከሀገር ውስጥ ዜጎች ጋር በትንንሽ ንግዶች ሊወዳደሩ እንደማይገባ አስገንዝበዋል። “ከውጭ ሀገር መጥቶ በኬንያ ሸቀጣሸቀጥ የሚቸረችር ወይም ሱቅ የሚከፍት ሊኖር አይገባም” ሲሉም ተናግረዋል።
ይህንን ውሳኔ በህግ ለማፅናት የሀገር ውስጥ ይዘት ረቂቅ ህግን በፓርላማ ማፋጠን መጀመሩ ተገልጿል። የቀረበው ረቂቅ ህግ የውጭ ኩባንያዎች ቢያንስ 80 በመቶ ሠራተኞቻቸው ኬንያውያን እንዲሆኑ፣ እንዲሁም ግብአታቸው በሀገር ውስጥ እንዲሸፈን የሚጠይቅ ነው። እርምጃው የሀገር ውስጥ ነጋዴዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና የኢኮኖሚ ዋስትናቸውን ለመጠበቅ ያለመ መሆኑ ታውቋል።SECO


