በአለምሰገድ እስጢፋኖስ
ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ስኬቶቹን የበለጠ ለማጉላት፣ ከማህበረሰቡ ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከርና ቀጣይ የትኩረት መስኮቹን ለማሳወቅ ከፊታችን ጥቅምት 2/2019 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ በአይነቱ ልዩ የሆነ ኤግዚቢሽንና ባዛር በመስቀል አደባባይ እንደሚያዘጋጅ አስታዉቋል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽንና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ሁናቸው ታዬ በሸራተን ሆቴል በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ተቋሙ ባለፉት 30 ዓመታት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
አሁን ላይ ከ45 በላይ ኩባንያዎችን በውስጡ የያዘው ግዙፉ ግሩፕ፤ በማኑፋክቸሪንግ፣ በግብርና፣ በሆስፒታሊቲ፣ በአገልግሎት፣ በኮንስትራክሽንና ሪልስቴት ዘርፎች ተሰማርቶ ከ80 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል።
በቢዝነሱ ዓለም ተወዳዳሪ ሆኖ ከመዝለቅ ባለፈ ከሚያገኘው ትርፍ 10 በመቶውን ለበጎ አድራጎት የሚያውለው ሚድሮክ፤ በሳለፈው በጀት ዓመት ብቻ ከ31 ቢሊዮን ብር በላይ ግብር በመክፈል ታማኝ ግብር ከፋይነቱን አሳይቷል። እንዲሁም አምርቶ ለውጭ ገበያ ባቀረበው ምርት ከ390 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ እንዳስገኘ አቶ ሁናቸው ገልጸዋል።
በሚዘጋጀው በዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር ሁሉም የሚድሮክ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው በመቅረብ የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩ እና ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቻቸውን እንደሚሸጡ ተገልጿል።SECO


