የቀድሞ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚና በአሁኑ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ፍሬሕይወት ታምሩ በአፍሪካ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ ጉልህ አሻራ ያሳረፉ 100 ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።
ይህ አህጉራዊ እውቅና በአፍሪካ ሃይፐርስኬለርስ (Africa Hyperscalers) እና ዘ ሊትልስቴፕስ ግሩፕ (The Littlesteps Group) ይፋ የተደረገ ሲሆን ሚኒስትሯ በቴሌኮም እና በመሰረተ ልማት ዘርፍ ግንባር ቀደም ሆነው የተመረጡት ኩባያችንን በማዘመን እና በማሳደግ ላሳዩት የላቀ አመራር ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሯ ፍሬህይወት ታምሩ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ለስምንት ዓመታት ተቋሙን የመሩ ሲሆን በቆይታቸው የኩባንያውን ደንበኞች ቁጥር ወደ 90.1 ሚሊዮን በማሳደግ፣ የ5ጂ (5G) አገልግሎትን በማስጀመር እና ቴሌብርን (telebirr) ወደ ሥራ በማስገባት ኩባንያውን በከፍተኛ ደረጃ እንዳዘመኑ ይነገርላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ሚኒስትሯ በስራ ዘመናቸው የቴሌኮም ተደራሽነትን በማስፋፋት፣ አስተማማኝ የዲጂታል መሰረት በመጣል እና የዲጂታል ፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ለሀገራዊ የዲጂታል ሽግግር ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል። ሚኒስትሯ በኢትዮ ቴሌኮም ከ 2010–2019ዓ·ም በነበራቸው ቆይታ በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ የአፍሪካ ምርጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ በቾይሱል 100 አፍሪካ የነገ የአፍሪካ የኢኮኖሚ መሪዎች ዝርዝር ውስጥ መካተታቸው ይታወቃል።SECO


