ከህዳር 10 ጀምሮ ሁሉም የጭነት ማስያዣና የባቡር መርሐ ግብር በዲጂታል ሥርዓት ብቻ እንዲከናወን አዟል
የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱን ወደ ሰፊ የሎጂስቲክስ እና መልቲሞዳል ጭነት አገልግሎት ለማሳደግ እየወሰደ ካለው እርምጃ ጋር በተያያዘ፣ ከህዳር 10 ጀምሮ ሁሉንም የጭነት ማስያዣና የባቡር የጊዜ ሰሌዳ ዝግጅት በዲጂታል ሥርዓት ብቻ እንዲከናወን አዘዘ።
በዚህም የባቡር ፉርጎዎችና ባቡሮች የሚመደቡት በድርጅቱ ዲጂታል መድረክ በኩል የተከናወነ የጭነት ማስያዣና የጊዜ ሰሌዳ ሲኖር ብቻ እንደሚሆን ድርጅቱ አስታውቋል።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ የፈረሙት የውስጥ መመሪያ፣ በዋናው መሥሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ለሚገኙ የኦፕሬሽን እና የንግድ ኃላፊዎች የተላከ መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ ከትልልቅ የንግድ ደንበኞች እስከ ግለሰብ ተጠቃሚዎች ያሉ ሁሉንም ደንበኞች ይመለከታል ተብሏል።
ETBusinessView ያየው የውስጥ ሰነድ እንደሚያመለክተው፣ አዲሱ መመሪያ የጭነት ማስተናገድ ጊዜን ለማሳጠር፣ የሥራ ሂደቶችን ለማቀላጠፍና የደንበኞችን አገልግሎት ለማሻሻል ያለመ ነው።
መመሪያው የጭነት ቦታ ማስያዣና የባቡር መርሐ ግብር ዝግጅት ከዲጂታል ሥርዓቱ ውጭ በእጅ/ማኑዋል የሚከናወንበት አሠራር ወዲያውኑ እንዲቆም ያዛል።
በተጨማሪም ነጠላ የትራንስፖርት አገልግሎትን (Unimodal) እና መልቲሞዳል የጭነት አገልግሎቶችን (Multimodal) የሚመለከቱ ሁሉም ግብይቶች በመድረኩ ወይም በዲጂታል መላ በኩል ብቻ እንዲከናወኑ ደንግጓል።
እርምጃው የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ከባቡር ትራንስፖርት ባሻገር የወደብ፣ የውስጥ ደረቅ ወደብና የጭነት ማከፋፈያ አገልግሎቶችን በማቀናጀት በክልሉ የሎጂስቲክስ ገበያ ያለውን ሚና ለማስፋት ከሚያደርገው ጥረት ጋር የተያያዘ መሆኑ ነው የተጠቀሰው።
በዚህ ረገድ ከተወሰዱ አስፈላጊ እርምጃዎች አንዱ በእንዶዴ የሚገኘው የገላን ሁለገብ ወደብ (Gelan Multipurpose Port) የጉምሩክ ፍተሻ እና የመልቲሞዳል ጭነት መዳረሻ እንዲሆን መፈቀዱ ነው። የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን የገላን ወደብን የጉምሩክ መዳረሻ አድርጎ ያፀደቀ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የማሪታይም ባለሥልጣንም የመልቲሞዳል ጭነት መዳረሻ እንዲሆን ፈቅዷል።
ይህ ፈቃድ የመርከብ ኩባንያዎች ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ኮንቴይነሮችን የመጨረሻ መዳረሻ ገላን ሁለገብ ወደብ እንዲያደርጉ ያስችላል። ጭነቶቹም በአንድ የትራንዚት የጭነት ሰነድ (Through Bill of Lading) በባቡር ወደ አገር ውስጥ ሲጓጓዙ፣ የጉምሩክ ሂደት በወደቡ እንዲከናወን ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡
ኩባንያው በተጨማሪም የጭነት ፉርጎዎችና የኤሌክትሪክ ሎኮሞቲቮች ብዛትን ለማሳደግ፣ ተጨማሪ የባቡር ምልልሶችን ለማልማትና የመልቲሞዳል አገልግሎቶቹን ለማጠናከር እየሠራ መሆኑ ይታወሳል፡፡SECO

