በቱርክ አንታሊያ ከተማ ለሁለት ሳምንታት ሲካሄድ የቆየው 31ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ጉባኤ (COP31) በሀገራት መካከል በተፈጠረ ጥልቅ ልዩነት ምክንያት ያለ ዋና ስምምነት መጠናቀቁን ቢቢሲ ዘግቧል።
በታሪክ ረጅሙ የተባለው ይህ ጉባኤ ያለ ውጤት የተበተነው፣ በቅሪተ-አካል ነዳጆች አጠቃቀም ቅነሳ እና በፋይናንስ ድጋፍ ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ነው። በመጨረሻው ረቂቅ ሰነድ ላይ ስለ ቅሪተ-አካል ነዳጆች በግልጽ አለመጠቀሱ የአውሮፓ ህብረትንና የፓስፊክ ደሴት ሀገራትን ክፉኛ አስቆጥቷል።
በሌላ በኩል ታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከበለጸጉ ሀገራት የሚጠበቀው ግልጽ የፋይናንስ ቃል አለመካተቱን ተቃውመዋል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በውጤቱ “በጥልቅ ማዘናቸውን” ገልጸው፣ የነዳጅ ኩባንያዎች ተጽዕኖ ሂደቱን ማደናቀፉን ተችተዋል። እንደ ሳውዲ አረቢያ እና ሩሲያ ያሉ ነዳጅ አምራች ሀገራት ደግሞ ከቅሪተ-አካል ነዳጅ በፍጥነት መውጣት የኃይል እጥረት እንደሚያስከትል ገልጸው ረቂቁን ተቃውመውታል።
የተመድ የአየር ንብረት ኃላፊ ሳይመን ስቲል የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱ መሻሻል እንደሚያስፈልገው ጠቁመው፣ በህዳር 2027 በኢትዮጵያ በሚካሄደው ቀጣዩ ጉባኤ (COP32) የተሻለ ውጤት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።seco


