የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት የተመራ የልኡኳን ቡድን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ እንደተገለጸው ባንኩ በትግራይ ክልል የኢንቨስመንት እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ እየሰራ ይገኛል፡፡
ባንኩ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን በመገንባት እንዲሁም በተጨማሪ አስቸኳይ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ በመስጠት ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተወካይና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪዩቲቭ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ገልፀዋል። ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ታደሰ ወረደ ባንኩ ባለፉት ዓመታት በትግራይ ክልል ለሚንቀሳቀሱ የንግድ ማህበረሰብ ያቀረበው የብድር መጠን በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ እገዛ አድርጓል ብለዋል።
ከጦርነቱ በኋላ በክልሉ የስራ አጥ ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነና ስራ አጥነትን ሊቀርፉ በሚችሉ የኮንስትራክሽንና ኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ የፋይናንስ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አማኑኤል አሰፋ በበኩላቸው በክልሉ በማህበር የተደራጁ ከ60 ሺ በላይ ቤት ፈላጊ ወጣቶች መኖራቸውን አንስተው ባንኩ ብድር ለወጣቶቹ እንዲያመቻች ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል የፌዴራል መንግስት በ”ኤፈርት” ስር በሚገኙ 22 ኩባንያዎች ላይ ተጥሎ የነበረውን የባንክ ሂሳብ እገዳ አንስቷል።
ይህም የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ደንበኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ሂሳባቸውን እንዲያንቀሳቅሱ የሚያስችል ሲሆን፣ የንግድ ባንክም በትምህርትና ጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ ላይ ያለውን ተሳትፎ እንደሚቀጥል አስታውቋል።@seco


