ራስ ገዟ ሶማሊላንድ፤ የአሜሪካ ልዩ ኃይል በቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ላይ የፈፀመውንና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደረገውን ወታደራዊ ኦፕሬሽን እንደምትደግፍ አስታወቀች።
ፕሬዝዳንት ማዱሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ቅዳሜ በአሜሪካ ጦር በካራካስ በተፈፀመ ድንገተኛ ጥቃት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ክስ ለመስማት ኒውዮርክ እንደሚገኙ ተገልጿል።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ የዋሽንግተን እርምጃ በቬንዙዌላ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚደረገው ዓለም አቀፍ ጥረት አካል መሆኑን ገልጿል። “የሶማሊላንድ መንግሥት በቬንዙዌላ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን እና ዴሞክራሲያዊ ህጋዊነትን ለመመለስ ከአሜሪካ ጎን መቆሙን ያረጋግጣል” ሲል ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
መግለጫው አክሎም፤ በአሜሪካ የሚመራው ይህ ጥረት ከቀጣናዊ እና ከባለብዙ ወገን አጋሮች ጋር በቅንጅት ከተከናወነ በላቲን አሜሪካዊቷ አገር ያለውን ሰብዓዊ እና የደህንነት ቀውስ ለመፍታት እንደሚረዳ ያምናል።
ይህ የሶማሊላንድ ድጋፍ፤ በታሪክ ከቀንድ አፍሪካ ጉዳዮች ውጭ በሆኑ ዓለም አቀፍ ኩነቶች ላይ ከምትሰጠው አስተያየት የተለየና ያልተለመደ መሆኑ ተመልክቷል። ይህም ሶማሊላንድ ከዋሽንግተን ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከርና ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት የምታደርገው ጥረት አካል ተደርጎ ተወስዷል።@SECO


