በኢትዮጵያ በፌዴራል ደረጃ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የንግድ ድርጅቶች ቁጥር ባለፈው የ2025 የፈረንጆቹ ዓመት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተገለጠ።
በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ባለሙያዎች የተዘጋጀው አምስተኛው የሥራ ገበያ ጥናት (Labor Market Intelligence) ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ በአገሪቱ ከነበሩት የንግድ ፈቃዶች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከምዝገባ የወጡ ሲሆን፣ ይህም ባለፉት አሥር ዓመታት የታየውን እድገት ወደ ኋላ የመለሰ ክስተት ሆኗል።
በ2024 በፌዴራል ደረጃ ተመዝግበው የነበሩ የንግድ ድርጅቶች ቁጥር ወደ 585,000 ይጠጋ የነበረ ቢሆንም፣ በ2025 ግን ይህ ቁጥር ወደ 100,000 ዝቅ ብሏል።
ይህ ድንገተኛ የንግድ ድርጅቶች ቁጥር መቀነስ በሁሉም የንግድ ዘርፎችና ደረጃዎች ላይ የታየ መሆኑ ዘገባውን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል። በጥናቱ መሰረት፣ ከ360,000 በላይ ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች፣ 90,000 የሚጠጉ አነስተኛ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከ23,000 በላይ መካከለኛ የንግድ ተቋማት ፈቃዳቸው ተሰርዟል።
አልፎ ተርፎም ከፍተኛ ካፒታል ያላቸው ትላልቅ ድርጅቶች ቁጥር በ86 በመቶ ቀንሶ ከ800 በታች መውረዱ ተጠቁሟል። ይህ የንግድ ተቋማት መዝጋት በንግድ፣ በአገልግሎት፣ በሎጂስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን እና በግብርና ዘርፎች ላይ እኩል ተጽዕኖ አሳርፏል።
ለዚህ አስደንጋጭ ቅናሽ እንደ ምክንያትነት የተጠቀሱት ሥርዓታዊ ችግሮች እንደሆኑ ተገልጿል። በተለይም በንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የተደረጉ የሕግ ለውጦች፣ የማክሮ-ኢኮኖሚ ተግዳሮቶች፣ የብድር አቅርቦት እጥረት፣ እንዲሁም ንቁ ያልሆኑ (Inactive) የንግድ ፈቃዶችን የማጽዳት አስተዳደራዊ እርምጃዎች ለውጤቱ መገኘት በምክንያትነት ተቀምጠዋል።
ይህ ሁኔታ በአገሪቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ስጋት የደቀነ ሲሆን፣ በተለይም አነስተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በሚሰማሩባቸው ጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፎች ላይ የሥራ አጥነት አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል ሲል የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነዉ።@SECO


