በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በምዕራብ ጎዴ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ለመጀመሪያ ጊዜ በመስኖ የለማውን የሩዝ ምርት የመሰብሰብ ሥራ በይፋ ተጀመረ።
ይህ የልማት እርምጃ ክልሉ ከሰብአዊ እርዳታ ጥገኝነት ተላቆ ራሱን በምግብ ለመቻል ለጀመረው ጉዞ ትልቅ ተስፋ የሰጠ ስኬት ተደርጎ ተወስዷል።
የምርት መሰብሰብ ሥራው እሁድ ዕለት በበርዓኖ ወረዳ የተጀመረ ሲሆን፣ በዕለቱም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በ35 ሄክታር መሬት ላይ የለማው የሩዝ ምርት መሰብሰብ ተጀምሯል።
ፕሮጀክቱ በክልሉ ግብርና ቢሮ የሚመራ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ 150 ሄክታር መሬት ለሩዝ እና ለስንዴ ልማት እንዲውል መደረጉ ታውቋል።
የክልሉ አመራሮች እና የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮች በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ይህ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በክልሉ የሚስተዋለውን የምግብ ዋስትና ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የታለመ ነው።
ደረቃማ የሆኑትን የቆላማ አካባቢዎች የዋቢ ሸበሌ ወንዝን በመጠቀም ወደ ልማት በማስገባት፣ ከውጭ የሚመጣን የምግብ እርዳታ ለመቀነስና የአገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ የገበያ መረጋጋት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።@SECO


