የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአደጋ ጊዜ የሚደረጉ ድጋፎችን በተቀናጀና በተቋማዊ መንገድ ለመምራት እንዲሁም “ከተረጂነት ወደ ምርታማነት” የሚደረገውን አገራዊ የፖሊሲ ሽግግር ለማገዝ “የአደጋ ስጋት ቅነሳ ምክር ቤት” በይፋ አቋቁሟል።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት (አዲስ ቻምበር) የዚህ ምክር ቤት አባል በመሆን የመጀመሪያውን ጉባኤ በከተማዋ አስተዳደር መሰብሰቢያ አዳራሽ አካሂዷል።
በምክር ቤቱ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ምክር ቤቱ የተቋቋመው ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን አስቀድሞ ከመከላከል ባለፈ፣ ልመናንና ተረጂነትን በማስቀረት ዜጎች በራሳቸው ጥረትና ድካም ለዘላቂ ልማት እንዲተጉ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ አክለውም፣ በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት የተረጂነትን አስተሳሰብ በመለወጥ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ አሳስበዋል።
አዲስ ቻምበር በበኩሉ በከተማዋ የሚገኘውን ከ482 ሺህ በላይ ሕጋዊ ነጋዴ የሚወክል አንጋፋ ተቋም እንደመሆኑ፣ በምክር ቤቱ ውስጥ አባላቱን በማስተባበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።
ምክር ቤቱ ለአደጋ መከላከልና ምላሽ አሰጣጥ የሚውሉ ግብዓቶችንና ፋይናንስን በንግዱ ማህበረሰብ በኩል በቅንጅት ለማሰባሰብ፣ ነጋዴው ማህበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ግንዛቤ ለመፍጠርና ባለፉት 78 ዓመታት ያከማቸውን የአደጋ ምላሽ ተሞክሮ ለምክር ቤቱ ስኬት ለማዋል አቅዷል።
የከተማ አስተዳደሩ በደንብ ቁጥር 191/2017 (እ.ኤ.አ 2025) መሠረት ያዋቀረው ይህ ምክር ቤት፣ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራርን ወደ ዘመናዊና በራስ ጥረት ላይ ወደተመሠረተ ሥርዓት ለማሸጋገር እንደ ሀገር የተጀመረውን የአሠራር ለውጥ በከተማዋ ለማስቀጠል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል።@SECO


