ኢትዮጵያና ሕንድ በቅመማ ቅመም እና በመድኃኒት ዕፅዋት ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በኢትዮጵያ የሕንድ ኤምባሲ ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ልዩ መድረክ ላይ፤ ሁለቱ ሀገራት የጀመሩት አጋርነት የኢትዮጵያን የወጪ ንግድ አቅም ለማሳደግ እና የሕንድን የላቀ የቴክኖሎጂ ተሞክሮ ለመጠቀም ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
በተለይም እንደ ዝንጅብል፣ እርድ፣ የተለያዩ ቅመማ ቅመሞች እና ማሽላ ባሉ ምርቶች ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ኤምባሲው ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ኢትዮጵያ ከፍተኛ እሴት የተጨመረባቸው እና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ወደ ውጭ ገበያ እንድትልክ ሕንድ በዘርፉ “በጥራት አብዮት” ያካበተችውን ሰፊ ልምድ የምታካፍልበት የቴክኒክ ድጋፍ ማዕቀፍም ተዘጋጅቷል።
ይህ አጋርነት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናን (AfCFTA) በመጠቀም የምሥራቅ አፍሪካ የምግብ ማቀነባበሪያ ማዕከል ለመሆን ለቀረፀችው ስትራቴጂ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ተመላክቷል።@SECO


