የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላትና ዓለም አቀፍ ደንበኞቹ በቀላሉና በሕጋዊ መንገድ የገንዘብ ዝውውር እንዲያደርጉ የሚያስችለውን “ሲቢኢ ኮኔክት ዲጂታል ዋሌት” የተሰኘ አዲስ የፋይናንስ አገልግሎት መድረክ በዛሬው ዕለት በይፋ አስመረቀ።
ይህ መተግበሪያ ባንኩ ከአገር በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያ ኢግልላይን ሲስተም ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ያበለጸገው ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላና አስተማማኝ ደኅንነት ያለው መሆኑ ተገልጿል።
አዲሱ መድረክ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ያለምንም የስዊች አገልግሎት አማካይነት ድንበር ተሻጋሪ የገንዘብ መላላክ እንዲያከናውኑ ከማስቻሉም በላይ፣ የውጭ ምንዛሪ እንዲሁም የቤትና የመኪና ብድር አገልግሎቶችን ለማግኘት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
መተግበሪያው እንደ ቪዛ እና ማስተርካርድ ያሉ ዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶችን በመጠቀም ገንዘብ ለመላክ የሚያስችል ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተጨማሪ ከሌሎች የአገር ውስጥ ባንኮች ሒሳብ ጋር በመተሳሰር ቅጽበታዊ የገንዘብ ዝውውር እንዲከናወን ያደርጋል።
ይህ አገልግሎት በተለይ ደንበኞች ሕገ-ወጥ የውጭ ምንዛሪ ገበያን ትተው ሕጋዊ መንገድን እንዲከተሉ በማበረታታት ለአገሪቱ የልማት ተግባራት የሚውል በቂ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እንዲኖር ታላቅ ድርሻ እንደሚኖረው በምረቃው ወቅት ተመላክቷል።
መተግበሪያው በይፋ ሥራ መጀመሩን ያበሰሩት የባንኩ የሥራ መሪዎች፣ ወደፊት አገልግሎቱ ለወጪ ንግድ ክፍያ፣ ለአነስተኛ ፋይናንስና ለነጋዴዎች አገልግሎት ጭምር እንዲውል ሆኖ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።@SECO


