የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ክሪፕቶ ከረንሲን ጨምሮ ፈቃድ በሌላቸው የተለያዩ መተግበሪያዎች የሚደረጉ የአቻ የዲጂታል ግብይቶች ማገዱን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በተዘረጉ የቁጥጥር ማዕቀፎች መሰረት በተደረገ ክትትል ግለሰቦች ከባንኩ ፈቃድ በሌላቸው የተለያዩ መተግበሪያዎች ግብይቶችን እየፈፀሙ እንደሆኑ ባንኩ ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጿል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል ግብይት ፍላጎት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ገባንኩ አስታውቆ ግለሰቦች ግብይት በሚፈፅሙበት ወቅት በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርተው ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በተለይም የዲጂታል ግብይቶች የገበያ ተለዋዋጭነትን፣ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ ማሳሳትን፣ የሳይበር ወንጀልን፣ የግብይት ግልፀኝነት ችግሮችን የሚያስከትሉ እንዲሁም የህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና የፋይናንስ ሽብርተኝነት ክልከላ ማዕቀፍ የሌላቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ባንኩ ዲጂታል የግብይት ቴክኖሎጂዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችል አጠቃላይ የቁጥጥር ማዕቀፍ በመዘርጋት እየሰራ መሆኑን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
የግብይት ቁጥጥር ማዕቀፍ ይፋ እስከሚሆን ድረስ ክሪፕቶ ከረንሲን ጨምሮ ፈቃድ በሌላቸው የተለያዩ መተግበሪያዎች የሚደረጉ የአቻ የዲጂታል ግብይቶች የተከለከሉ መሆኑን ባንኩ በመግለጫው አስታውቋል፡፡@SECO


