የቴክኖሎጂው ግዙፍ ኩባንያ ጎግል (Google)፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የሚጠቀምባቸውን ‘AI Overviews’ እና ‘AI Mode’ የተሰኙ የፍለጋ መተግበሪያዎቹን በ13 የአፍሪካ ቋንቋዎች ማበልጸጉን ይፋ አደረገ።
በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን በራሳቸው ቋንቋ መረጃዎችን የመፈለግ፣ የመማርና የመፍጠር ዕድል ያገኛሉ።
ከአፍሪካ ከተመረጡት 13 ቋንቋዎች መካከል የኢትዮጵያዎቹ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ የሚገኙ ሲሆን፣ በተጨማሪም ስዋሂሊ፣ ሱማሊኛ፣ ዙሉ እና ዮሩባ በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል።
ተጠቃሚዎች በ ‘AI Overviews’ አማካኝነት ስለፈለጉት ጉዳይ አጭርና ግልጽ የሆነ በ AI የተዘጋጀ ማጠቃለያ ከታማኝ የመረጃ ምንጮች ጋር የሚያገኙ ሲሆን፣ በ ‘AI Mode’ ደግሞ በጽሑፍ፣ በድምፅ ወይም በምስል ጥያቄዎችን በማቅረብ ጥልቅና ዝርዝር ምላሾችን በራሳቸው ቋንቋ ማግኘት ይችላሉ።
የጎግል ደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ካቤሎ ማክዋኔ እንደገለጹት፣ ቴክኖሎጂ ዓለም አቀፍ የበላይነት ባላቸው ቋንቋዎች ብቻ ሲወሰን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያገል በመሆኑ፣ ይህ እርምጃ አፍሪካውያን የ AI ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ቴክኖሎጂውን ለራሳቸው ፈጠራና ለማኅበረሰባቸው ችግር መፍቻ እንዲያውሉት ያግዛቸዋል ተብሏል።
ይህ ስኬት የተገኘው የቋንቋ ጥናትንና የቴክኖሎጂ ምርምርን አጣምሮ በያዘው የጎግል ‘ዋክሳል’ ፕሮጀክት አማካኝነት ሲሆን፣ ቋንቋዎቹ የተመረጡትም በአህጉሪቱ በሰፊው ጥቅም ላይ እየዋሉ ባሉበት ሁኔታ ላይ ተመስርቶ መሆኑ ተጠቁሟል።
ተጠቃሚዎች በስልካቸው ላይ ያለውን የጎግል መተግበሪያ በመክፈትና ‘AI Mode’ የሚለውን ምልክት በመጫን ጥያቄዎቻቸውን በራሳቸው ቋንቋ በመጠየቅ አገልግሎቱን መጠቀም እንደሚችሉ ተገልጿል።@SECO


