በአለምሰገድ እጢፋኖስ
የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የመንግስትና የግል ዘርፍ የምክክር ፎረም አካሂዷል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት አምራች እንደስትሪው ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች በማምረት የውጭ ምንዛሬን ወጪ መቀነስ ያስችላሉ፡፡
ባለሀብቶች ኢንቨስት በማድረግ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን ከመወጣት በዘለለ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በሚያደርጉት ጥረት የቦታና የፋይናንስ አቅርቦት እንቅፋት እንደሆነባቸው ነው የተናገሩት ፡፡
ከመሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ መሬት የሊዝ ዋጋ ውድ መሆን ለዘርፉ እንቅፋት ሆኖ እንደቀጠለ በባለሀብቶች ተነስቷል፡፡

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ እንደገለጹት አምራች ኢንደስትሪው በቂ የፋይናንስና አቅርቦትና መስሪያ ቦታ ሊመቻችለት ይገባል፡፡
ባንኮች የሚያቀርቡት የብድር መጠን አነስተኛ መሆንና የሚያቀርቡት ብድር ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተ በመሆኑ አምራች ድርጅቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዳይገቡ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የፋይናንስ አቅርቦት እጥረት ለንግዱ ማኅበረሰብ 40 በመቶ የሚሆነውን ማነቆ ሲይዝ የመሬትና የመሥሪያ ቦታ አቅርቦት እጥረት ሌላኛው ተጠቃሽ ችግር እንደሆነ አንስተዋል።
የፋይናንስ አቅርቦትን ማመቻቸትና የብድር አሰጣጥ ሥርዓትን በማሻሻል ምቹ የንግድ ከባቢ ለመፍጠር መሰራት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
ምክር ቤቱ በንግድ ዘርፉና በኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚታዩ የአመለካከት፣ የፋይናንስ እና የመመሪያ ማነቆዎችን ለመቅረፍ ጥረት እየደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ስራ ፈጠራ ልማት ኢኒስቲትዩት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሃሰን ሁሴን (ዶ/ር) የመሬት እና የፋይናንስ አቅርቦት ነጋዴዎች የጀመሩትን ስራ ለማስፋፋትም ሆነ አዳዲስ ስራ ፈጣሪዎች እንዳይኖሩ እንቅፋት እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡
የአመለካከትና የክህሎት ክፍተቶች ለዘርፉ እድገት መቀጨጭ ምክንያት እንደሆነ ጠቁመው በመንግሥትና በነጋዴው መካከል ያለው ግንኙነት ከጥርጣሬ ወጥቶ ወደ ተሻለ አጋርነት ሊቀየር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ሰዎች በቀላሉ ንግድ እንዳይጀምሩ ወይም የጀመሩትን እንዳያስፋፉ የሚያደርጉ የሕግና የመመሪያ ማነቆዎች መኖራቸውንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል።@SECO


