የዩክሬን ብሔራዊ የኃይል ተቋም ናፍቶጋዝ በጥቁር ባሕር ላይ የሚገኝና ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበትን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በጋራ ለማልማት ከሮማኒያው ኦኤምቪ ፔትሮም ጋር የመጀመሪያ ደረጃ ውይይት መጀመሩ ተገለጸ።
ይህ ፕሮጀክት አውሮፓ ከሩሲያ የሚመጣባትን የተፈጥሮ ጋዝ ጥገኝነት ለመቀነስ ለምታደርገው ጥረት ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል።
እንደ ዘገባዎች አመላካችነት፣ ይህ የጋዝ ክምችት ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ በፊት በናፍቶጋዝ የተገኘ ሲሆን፣ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችም ክምችቱን በጥቁር ባሕር ቀጠና ካሉ እጅግ ተስፋ ሰጪ የጋዝ መገኛዎች አንዱ እንደሆነ ይገልጹታል።
ይሁን እንጂ የውይይቱ ሂደት ገና በጅምር ላይ ያለ በመሆኑና በአካባቢው ያለው የጸጥታ ስጋት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር የሚገባበትን ጊዜ እርግጠኛ እንዳይሆን አድርጎታል።
መጠነ ሰፊ የልማት ሥራው ሊጀመር የሚችለውም ጦርነቱ ሲቆም እንደሆነ ተጠቁሟል።
ይህ ሊጀመር የታቀደው የጋዝ ልማት ፕሮጀክት ኪየቭና ቡካሬስት በኃይል፣ በመሠረተ ልማትና በመከላከያ ዘርፎች ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እያጠናከሩ ባሉበት ወቅት የቀረበ ነው።
ባለፈው ሳምንት በሮማኒያ ዋና ከተማ በተካሄደው ስብሰባ፣ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ እና የሮማኒያው ፕሬዝዳንት ኒኩሶር ዳን የድንበር ተሻጋሪ መሠረተ ልማቶችንና የኃይል ትብብርን የሚያካትት ስትራቴጂካዊ የአጋርነት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።@SECO


