“ያልተገባ ተጽዕኖ ባለባቸው አካባቢዎች ምርጫውን እስከ መሰረዝ እንገደዳለን” — የምርጫ ቦርድ ማስጠንቀቂያ

በኢቢቪ ዘጋቢ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ እየታዩ ያሉ የሕግ ጥሰቶችን አስመልክቶ በሰጠዉ መግለጫ፣ ያልተገባ ተጽዕኖ በሚታይባቸው አካባቢዎች ምርጫውን እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠነቀቀ።

ቦርዱ እንዳመለከተው፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ከመመሪያ ውጭ የሆኑና የዜጎችን መብት የሚጋፉ ተግባራት እየተፈጸሙ መሆኑን የሚያሳዩ ሪፖርቶች ደርሰውታል።

በተለይም በቤት ለቤት ቅስቀሳ ዜጎች ያለፍላጎታቸው እንዲመዘገቡ ተጽዕኖ መፍጠር፣ የምርጫ ካርድ መውሰድን እንደ ግዴታ በመቁጠር ካልተመዘገቡ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን እንደማያገኙ ማስፈራራት እና “ካልተመዘገባችሁ ደመወዝ ይቆረጣል” በሚል ሠራተኞችን በሥራ ገበታቸው ላይ ማስገደድ የሚሉ ዋና ዋና የሕግ ጥሰቶች መታየታቸውን ቦርዱ በዝርዝር አሳውቋል።

የመራጮች ምዝገባ የዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንጂ ግዴታ አለመሆኑን የገለጸው ቦርዱ፤ በሁሉም የክልል መንግሥታትና በሁለቱ የከተማ መስተዳድሮች ሥር የሚገኙ አስፈጻሚዎች ከቤት ለቤት ቅስቀሳ እንዲቆጠቡና በዜጎች ላይ የሚደረጉ ያልተገቡ ጫናዎች በአስቸኳይ እንዲቆሙ በጽሑፍ አሳስቧል።

ማንኛውም አካል በነዋሪዎችም ሆነ በሠራተኞች ላይ የምዝገባ ካርድ እንዲወስዱ የማስገደድ ሥልጣን እንደሌለው ያስገነዘበው ቦርዱ፣ ይህን የሚያደርጉ ተቋማትንና አካላትን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል።

ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን የገለጸው ቦርዱ፣ የማስተካከያ እርምጃ ካልተወሰደ ያልተገባ ተጽዕኖ በሚታይባቸው የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ላይ ምርጫው እንዳይካሄድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ ውሳኔ ለመስጠት እንደሚገደድ አስጠንቅቋል።

ዜጎች መመዝገብ መብታቸው እንጂ ግዴታቸው አለመሆኑን ተገንዝበው፣ በራሳቸው ፍላጎትና ውሳኔ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ ቦርዱ ጥሪውን አቅርቧል።@SECO

Related

አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ  ሀላፊዎች ከኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሀላፊነታቸው ተነሱ

ድርጅቱን በቦርድ ሊቀመንበርነት ሲመሩት የነበሩት አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ፣ምክትል  ሰብሳቢ...

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተሰጠው የእገዳ መመሪያ ውዝግብ አስነሳ​​

በኢትዮጵያ የሰራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ...

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች የሦስት እርከን የደመወዝ ጭማሪ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጸደቀ

የሀገሪቱ ግዙፉ መንግሥታዊ የፋይናንስ ተቋም የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ...

አዳማ  የፈጣን ስማርት የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ መሙያ  ተጠቃሚ  ሆነች

በአለምሰገድ እስጢፋኖስ ኢትዮ ቴሌኮም በዛሬው ዕለት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ...

የኢትዮጵያ የሚዲያ ልህቀት ማዕከል ተመረቀ

“ከማገዳችን በፊት ከአምስቴ በላይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተናል!” የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ያስመረቀው...

Popular Categories